ምሩቃኑ የቀሰሙትን እውቀት ተጠቅመው የአገርን አንድነት ለማጎልበት ተዘጋጅተዋል

24
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 16/2011 በትምህርት ያገኙትን ሁሉን አቀፍ እውቀት በመጠቀም ኀብረተሰቡ አንድነቱን አጎልብቶ ኢትዮጵያዊነትን እንዲላበስ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ተናገሩ። ምሩቃኑ በንባብና በትምህርት ያገኙት እውቀት ጎጠኝነትን በመፀየፍ ለአንድነት እንዲተጉ የሚያደርግ መሆኑን ነው የገለፁት። ወቅቱ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 'የእኔ ብቻ ይሰማ' የሚል ስሜት እየተንፀባረቀ፤ አገር በተሳሳተ መስመር እንድትጓዝ የሚታትሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች እየተስተዋሉ ያሉበት ነው። ተመራቂዎቹ እነዚህ ግለሰቦችና ኃይሎች አገር እንድትፀናና አንድነትም እንዲጠናከር ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡና የአገሩን ጉዳይ ለህዝቡ ሊተዉለት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሰው ልጆች ሁሉ ከአንድ ዘር የመጡ መሆናቸውን በመገንዘብና ልዩነትን በመተው ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ መጣር አለብን የሚል አስተያየትም ሰንዝረዋል። ተመራቂ ተማሪ ዳዊት ፀደቀ “ሁላችንም የመጣነው ከአንድ እናትና ከአንድ አባት ነው፤ ሁሉም ሰው የመጣው ከአዳምና ከሄዋን ነው። ስለዚህ ማንኛችንም ብንሆን እከሌ ከዚህ ብሄር፣ እከሌ ከዚህ ብሄር ሳንል አንድ ኢትዮጵያዊነትን ይዘን ወደፊት መሻገር ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ።” ብሏል፡፡ ተመራቂ ተማሪ ቤዛዊት ካሳሁን በበኩሏ ሁላችንም አንድ የሚያደርገን ምንድነው ከአዳምና ከሄዋን እንደተፈጠርን ነው ሁላችንም አንድ ነን የመከፋፈሉ አሁን ያለው ሁኔታ ደስ አይልም ስትል አስተያየቷን ሰጥትታለች፡፡ "አገሬን በራሴ እመስላታለሁ የእያንዳንዱ የሰውነት ክፍሌ ጤንነት ለእኔ መኖር ዋስትና እንደሆነ የእያንዳንዱ ዜጋ አንድነት ለአገር መኖር ዋስትና ነው" ትላለች - ተመራቂዋ ሙሉጎጃም አስማማው። በመሆኑም ለአገር አንድነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበትም አክላለች። ምሩቃኑ ስለ አገር አንድነት በንባብና በትምህርት ያገኙትን እውቀት ከቤተሰቦቻቸው በመጀመር ለህብረተሰቡ በማጋራት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። ኀብረተሰቡ ቀና አስተሳሰብ በመያዝ መረጃዎችን መዝኖ መቀበል እንዳለበትና በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን የበለፀገች ለማድረግ እንዲሰራ፣ የመከፋፈል ችግሮችን ከቤቱ ጀምሮ ለመፍታት እንዲጥር አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም