በዞኑ ከ53ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በኩታ ገጠም ሊለማ ነው

71
መቀሌ ሰኔ 4/2010 በትግራይ ደቡብ ምስራቅ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት ከ53ሺህ ሄክታር የሚበልጠውን መሬት በኩታ ገጠም  ስንዴ ለማልማት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። አስተያየታቸውን  የሰጡ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ያገኙትን ስልጠና በመጠቀም ለመኸር እርሻ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የእርሻና ኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ መብራህቱ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በስንዴ አብቃይነቱ በሚታወቀውን የትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ስንዴ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በማልማትና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ በእዚህም በዞኑ በተያዘው የመኸር ወቅት በልዩ ልዩ ሰብሎች ለመሸፈን ከታቀደው 113ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉን በዳቦ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ እንደ አማካሪው ገለጻ፣ በማምረቱ  ሥራ  ለሚሰማሩ ከ12 ሺህ 300 በላይ አርሶ አደሮች የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና አግኝተዋል፡፡ በማዳበሪያ አጠቃቀም፣ በመስመር መዝራት፣ የአፈር እርጠበትን ይዞ በማቆየት፣ በጸረ አረም ተባይ አጠቃቀምና በመሳሰሉት የእርሻ ስራዎች ላይ በተግባር የተደገፈ ስልጠና መሰጠቱንም ነው ያስረዱት። በዚህም በዞኑ ከአንድ ሄክታር እየተገኘ ያለውን 19 ኩንታል ምርት ወደ 27 ኩንታል ከፍ  ለማድረግ መታቀዱንም  አስታውቀዋል። በልማት ቡድን የተደራጁት አርሶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑም በግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል። እንደ አቶ መብርሀቱ ገለጻ አርሶ አደሮች ከሚያመርቱት የስንዴ ምርት ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነውን ለዱቄት ፋብሪካዎች ለማቅረብ በሕብረት ሥራ ማህበራትና በፋብሪካዎች መካከል ስምምነት ተደርጓል፡፡ በዞኑ የደጉዓ ተምቤን ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረመድህን አብርሃ በበኩላቸው በተግባር ያገኙትን ስልጠና በመጠቀም በኩታ ገጠም ስንዴ ለማልማት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በዝናብ መቆራረጥ ምክንያት ከአንድ ጥማድ መሬት ከ17 ኩንታል ያልበለጠ የስንዴ ምርት ማግኘታቸውን ያስታወሱት አርሶ አደሩ፣ "ዘንድሮ የተሻለ ዝግጅት በማድረጌ ከሁለት ጥማድ የእርሻ መሬት የተሻለ የስንዴ ምርት ለማግኘት እየሰራሁ ነው" ብለዋል፡፡ በኩታ ገጠም የስንዴ ሰብል ለማልማት ሁለት ኩንታል ምጥን ማዳበሪያ መግዛታቸውን የተናገሩት ደግሞ  የሳህርቲ ሳምረ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ወልደብርሀን ታደለ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ከእዚህ ቀደም በእርሻ መሬታቸው ባቄላ፣ ስንዴ፣ ገብስ በመዝራት በዓመት ከ30 ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ ነበር። ዘንድሮ ከተለምዶ የግብርና ሥራ በመውጣት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴና ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን ተጠቅመው ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት በማድረጋቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም