በሰሜን ወሎ 80 ሺህ የገጠር ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ ሆኑ

64
ወልድያ ኢዜአ ሐምሌ 15 /2011  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 80 ሺህ የገጠር ነዋሪዎችን የንፁህ መጠጥ ውሀ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን የሰሜን ወሎ ዞን ውሃ፣መስኖና ኢነርጅ ልማት መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የእቅድ ዝግጅት ባለሙያ ወይዘሮ እመቤት ሞላየ ለኢዜአ እንደገለፁት ነዋሪዎቹን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው በ42 ሚሊዮን ብር ወጭ ግንባታቸው የተጠናቀቀ  466 አዲስ የውሀ ተቋማት ስራ በመጀመራቸው ነው ። ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት የውሀ ተቋማት ጥልቅና መለስተኛ ጉድጓዶች እንዲሁም የእጅ ፓምፓችና የጎለበቱ ምንጮች ናቸው። ለተቋማቱ ግንባታ ከዋለው ገንዘው ውስጥ ከ8  ሚሊዮን ብር በላይ ህብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ፣ በቁሳቁስ አቅርቦትና በጉልበት ባደረገው ተሳትፎ የተገኘ ነው። ባለሙያዋ "ተቋማቱ ዘለቄታ ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ወጣቶችን በጥገና በማሰልጠንና የመለዋወጫ እቃዎች በማቅረብ ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲያስተዳድራቸው ተደርጓል" ብለዋል ። እንደ ባለሙያዋ ገለፃ በተገነቡት ተቋማት የዞኑ የገጠር ንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ሽፋን ከነበረበት 78 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 84 በመቶ አድጓል። አርሶ አደር አበበ በላይ በዞኑ አንጎት ወረዳ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ከዚህ ቀደም ሴቶች ሁለት ሰዓት የፈጀ ደርሶ መልስ በመጓዝ በሚቀዱት ንፅህናው ያልተጠበቀ ወራጅ ውሃ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። "በአካባቢያችን የተገነባ የውሀ ተቋም አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ የሴቶቹም ድካም ቀርቷል፤ከውሀ ወለድ በሽታ ስጋትም ተላቀናል" ብለዋል። "ከዓመት በፊት ንጽህና የጎደለው የወንዝ ውሀ በመጠቀማችን በውሀ ወለድ በሽታ እንጠቃ ነበር" ያሉት ደግሞ በግዳን ወረዳ የቀበሌ 11 ነዋሪ ቄስ ሙላት በሪሁን ናቸው። መንግስት ጥያቄያቸውን ሰምቶ ምላሽ መስጠቱን አመልክተው በአካባቢያቸው በተገነባላቸው የጎለበተ ምንጭ ንፅህናው የተጠበቀ የቧንቧ ወሀ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል ። እንደ ቄስ ሙላት ገለፃ 70 የአካባቢው አባወራዎች የንፁህ መጠጥ ውሀ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው ከውሀ ወለድ በሽታ ተጋላጭነት ተላቀዋል ። በአካባቢያቸው የተገነቡላቸው የውሀ ተቋማት ከበሽታ ተጋላጭነት ስጋት ያላቀቋቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገልፀዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም