የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጸጥታ ሥራ በግዜያዊ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ ተወሰነ

381

ሐምሌ  15/2011 የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና  ህዝቦች ክልል  ሁሉም ዞኖች፣ ሀዋሳ ከተማ  አስተዳደርና ልዩ ወረዳዎች የጸጥታ ሥራው በፌዴራልና በጸጥታ ሃይል ቁጥጥር ሥር ሆኖ  ከዛሬ ጀምሮ በግዜያዊ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑ ተገልጿል።

የክልሉ መንግስት ያወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፤ የህግ የበላይነት በአግባቡ እንዳይከበር  እንቅፋት መሆኑና የዜጎች ደህንነት ጥያቄ ላይ በመውደቁ  የክልሉ መንግስት በጠየቀው መሰረት ከሐምሌ 15/2011 ዓ.ም ጀምሮ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ የፌዴራል የጸጥታው ምክር ቤት ወስኗል።

በክልሉ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት በንብረትና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ፤ያልተፈቀዱ ሰልፎችና የክልሉን ጸጥታ የሚያውኩ እንቅስቃሴዎች እንደሚስተዋሉም ነው በመግለጫው የተጠቀሰው፡፡

ስለሆነም በክልሉ ሰላምና ደህንነት ለማስፈን እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንዲቻልም ከሐምሌ  15/2011 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉ በፌዴራልና በጸጥታ ሃይል ቁጥጥር ሥር ሆኖ በግዜያዊ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑን የዘገበው የደቡብ መገናኛ ብዙሃን ነው፡፡

ዝርዝሩ  በቀጣይ ይፋ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡