በሀገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማስፈን እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

145

ድሬዳዋ ሐምሌ 15/2011 በሀገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማስፈንና አጋር የሚለው ፖለቲካዊ አሰራር መለወጥ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት የሀገረ- መንግሥት ግንባታና ብሔራዊ መግባባት በኢትዮጵያ በሚል ሃሳብ በድሬዳዋ ዛሬ የተጀመረው  ውይይት ተጠናቋል፡፡

“የብሔራዊ ግንባታ ውጣ ውረድ በኢትዮጵያ” .. በሚል ሀሳብ  ፅሁፍ ያቀረቡትና በኢንስቲትዩት ኦፍ ሰኪዩሪቲ ስተዲስ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር  ሰሚር ዩሱፍ  እንደተናገሩት ሁሉን አቀፍ ፈርጀ ብዙ የሰለጠነ ውይይት ማድረግ የጋራ ዓላማና ስጋትን በመካፈል ወደ ብሔራዊ ጉዳይ ያመራሉ ፡፡

ሌላው ፅሁፍ አቅራቢ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር  ኮንቴ ሙሳ በበኩላቸው በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ማስፈን መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

“እንደ ቤኔሻንጉል ፣ አፋር ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪና ጋምቤላ የመሳሰሉትን አጋር በሚል የፖለቲካ አሰራር ማሳተፍ ሀገር ለመገንባትና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ስለማያስችል በፍጥነት መለወጥ ይገባል “ብለዋል፡፡

የህግ የበላይነት እንዲከበር ዜጎች ህግን አክብረው የመንቀሳቀስ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶክተሩ ገለፃ ማህበራዊ ሀብትና ሥልጣንን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ነው፤ የህዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመለስ በሚችሉ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዕውቀት፣ ሃብትንና ጊዜን ማፍሰስ ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ናቸው ፡፡

የተበዳይነትን ስሜት ከውስጥ መግፈፍ ለሀገር ዕድገትና ብሔራዊ መግባባት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የሰላም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ናቸው።

ስለሌላው ማሰብ ፣ አብዝቶ ተስፋ በመሰነቅና በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ ከቤተሰብ ጀምሮ የዕርቅን እሴት በመተግበር ለሀገር ግንባታ የራሱን ሚና መጫወት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ ምሁራንና የምስራቅ ተጎራባች ነዋሪዎች ዜጎች፣ ባለሙያዎች ፣ ፖለቲከኞች ፣ የኃይማኖት ተቋማት ሁላቸውም ያለባቸውን  ኃላፊነትና ተግባር ከተወጡ  የሀገር እድገትና ብሔራዊ መግባባትን በቀላሉ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በሀገር ዋና ዋና  ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ፈጥሮ ለሁሉም የምትበጅ ሀገር ለመገንባት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

ተሳታፊዎቹ በውይይቱ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ሀገር ለመገንባትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንደሚሰሩ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡