በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የደረሰውንቃጠሎ ለማካካስ ከ38 ሺህ በላይ ችግኞች ተተከሉ

251

ኢዜአ ሀምሌ 15/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ደጋማው ክፍል በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የደረሰውን ውድመት ለማካካስ ከ38 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አበባው አዛናው እንደገለፁት የችግኝ ተከላው በተያዘው ዓመት መጋቢትና ሚያዚያ ወር በፓርኩ ውስጥ በደረሰው የእሳት አደጋ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመተካት ነው፡፡

ችግኞቹ የተተከሉትም ከክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ ሁለት ሺህ በሚደርሱ ወጣቶችና የዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ አባላት በማሳተፍ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተተከሉ  ያሉ ችግኞች በፍጥነት የሚያድጉና ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የችግኝ ተከላውም በፓርኩ ውስጥ ሳንቃ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ19 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት እንደተተከለም አስታውቀዋል፡፡

አሁን የተተከሉ ችግኞችን በቂ እንክብካቤ በማድረግና በቀጣይም በተመሳሳይ ይለማል ተብሏል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተቀባ ተባባል በበኩላቸው ዛሬ ፓርኩን መልሶ ለማልማት በተደረገው እንቅስቃሴ ልክ በቀጣይ በሀገር ሀቀፍ ደረጃ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

‹‹ለህዝብ ክብር ሲያገለግሉ የነበሩ አመራሮችን ለማሰብ ለሀገር በሚጠቅም ስራ በመሳተፍ አሻራችን ማስቀመጥ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የመጡት አቶ ይርጋለም አምሳሉ በዚህ የአለም ቅርስ በሆነው ቦታ መጥተው ችግኝ መትከል በመቻላቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

አደጋ ደረሰበት በተባለ ጊዜ የተሰማቸውን የልብ ስብራትም የፓርኩን የቀደመ ስነ-ምህዳር ለመመለስ ወጣቶች ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት ባደረጉት ተሳትፎ መጠገኑንም አንስተዋል፡፡

ፓርኩ አጋጥሞት በነበረው የእሳት አደጋም ከ1ሺህ ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ይታወቃል፡፡

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከ60 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን በተካሄደ እንቅስቃሴ አብዛኛውን ማሳካት እንደተቻለ ተመልክቷል፡፡

ዛሬ  በተካሄደው የተከላ መርሃ ግብርም የክልል፣ የዞንና ሜትሮፖሊታንት ከተሞች የተወጣጡ አመራሮችና የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከባህር ዳር፣ ከጎንደር፣ ከደብረታቦር፣ ደብረማርቆስና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቦችና የመንግስት ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡