ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ አስፈላጊው ዝግጅት እየተከናወነ ነው- ብሔራዊ የችግኝ ተከላ ቴክኒክ ኮሚቴ

254

ሐምሌ 15/2011 በመጪው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ለታቀደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን የብሔራዊ የችግኝ ተከላ ቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።

ኮሚቴው ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመሆን የፌደራል መስሪያ ቤቶችና ተቋማት በእለቱ በአዲስ አበባ ዙሪያ ስለሚተክሉት ችግኝ ዛሬ  ገለጻ ተደርጓል።

በዚህ ጊዜ የብሔራዊ ችግኝ ተከላ ቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ጌታቸው ግዛው እንደገለጹት በመጪው ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው  አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም ችግኞቹ የሚተከሉባቸው ቦታዎች ልየታ፣ የጉድጓድ ቁፋሮ፣ የችግኝ ማዘጋጀትና የመረጃ ልውውጥ የሚደረግባቸው አደረጀጃቶችን የመፍጠር ስራዎች ከተከናወኑት ቅድመ ዝግጅቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በፌደራል መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት የሚገኙ ከ31ሺህ በላይ ሰራተኞች በእለቱ ከ353 ሺህ በላይ ችግኝ ለመትከል የሚያስችላቸውን  ተግባር  እያከናወኑ ነው።

በእለቱ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን እቅድ ማሳካት ይቻል ዘንድ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል ሲሉም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው እንደተናገሩት የ”አረንጓዴ አሻራ” ለተሰኘው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬት ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት።

በእለቱ መላው ህዝብ አካፋና ዶማ ይዞ በመውጣት በችግኝ ተከላው በንቃት እንዲሳተፍም አቶ ዳባ ጠይቀዋል።

ተቋማት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ለሰራተኞቻቸው በማሳወቅ፣ የጎደለ ችግኝ ካላ በማሟላትና ችግኞቹ ከተተከሉ በኋላም ለሁለት ዓመት አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ውል መግባት ይኖርባቸዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ችግኞቹ በሚተከሉባቸው ቦታዎች ላይ ያሉትን እንቅስቃሴዎች በምስል መያዝና፣ከወረዳ እስከ ፌደራል ለተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በየሶስት ሰዓቱ መረጃ ማቀበል በእለቱ የሚጠበቁ ስራዎች ናቸውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተያዘው የክረምት ወቅት እስከ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

እስካሁን ህንድ 66 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ቀን በመትከል ክብረ ወሰን የያዘች አገር ስትሆን ኢትዮጵያ በመጪው ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ክብረወሰኑን ለመስበር አቅዳ እየሰራች ነው።