በኦሮሚያ ክልል 200 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት የእንስሳት ኃብት ልማት ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

79
ሐምሌ 15/2011 በኦሮሚያ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ የእንስሳት ኃብት ልማት ለማካሄድ የሚያስችልና 200 ሚሊዮን ብር ወጪ የተመደበለት ፕሮጀክት ሊተገበር ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቱን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የሶስትዮሽ ስምምነት ዛሬ ፈርመዋል። በምዕራብ ኦሮሚያ ቡኖ በደሌ፣ ኢሊባቡር፣ ጅማ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ተግባራዊ የሚደረገው ይህ ፕሮጀክት የወተት ልማት፣ የእንስሳት መኖ ዝግጅት፣ የእንስሳት ማዳቀል እና የስጋ ምርት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡ ወደፊትም ፕሮጀክቱ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ከኢንደስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ስራም ይሰራል ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ ከ500 በላይ በሚሆኑ የወተት ላሞች እና በ100 የስጋ ከብቶች ላይ በመነሻነት እንደሚጀመርም ታውቋል። ለፕሮጀክቱ የሚፈለገውን ወጪ የሚሸፍኑት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎች ሚኒስቴር፤  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ናቸው። ፕሮጀክቱ ወደስራ ሲገባ ለ35 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂኒየር ጌታሁን መኩሪያ እንደተናገሩት የእንስሳት ሃብት ልማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ አርሶ አደሩ ከሃብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር በትኩረት መስራት ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ጥናቶችን ሲያደርግ መቆየቱንና በእንስሳት ሃብት ልማት የሚታየውን የቴክኖሎጂ ክፍተት ለመሙላትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በፊት በትግራይ እና በሶማሌ ክልል የተተገበሩ ሙከራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኢኮኖሚ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ሰፊ የእንስሳት ሃብት ያለው የኦሮሚያ ክልል የሃብቱን ያህል ተጠቃሚ አይደለም፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቅንጅት መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በክልሉ 42 በመቶ የሚሆነው ህዝብ አርብቶ አደር መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ግርማ ይህንን የእንሳሳት ኃብት ልማት በቴክኖሎጂ በማገዝ ህብረተሰቡን ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ ማምጣት እንደሚቻልም ገልፀዋል። ዘርፉን ጥቅም ላይ ለማዋል የእንስሳትን ዝርያ መለየት፤ የመኖ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት እና የእንስሳት ምርቶችን በቴክኖሎጂ ማቀነባበር የግድ መሆኑንም ተናግረዋል። ዘርፉን ለአገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጪ ገቢያ በማቅረብ የአገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል። ስምምነቱ የፈረሙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂኒየር ጌታሁን መኩሪያ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮምያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የገጠር ልማት ሴክተር ሃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ተካልኝ ቀጄላ ናቸው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም