ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ ተካሄደ

106
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 15/2011 በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት 'ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ' በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ትላንት ተካሄደ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ባለፈው ዓመት የሰሜን አሜሪካ ሶስት ከተሞችን መጎብኘታቸው ይታወሳል። በዚሁ ወቅትም በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ ኢትዮጵያን ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በተዘጋጀላቸው አቀባበል ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት  የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከንቲባም እለቱ 'የኢትዮጵያ ቀን' ሆኖ እንዲሰየም  መወሰኑን አስታውቀዋል። ቀኑን በማስመልከትም ትላንት ሀምሌ 14 ቀን 2011 ዓም በዋሽንግተን ዲሲ 'ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ' በሚል ውድድር ተካሂዷል። በዚሁ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፈዋል። ከሩጫ ውድድሩ አዘጋጆች መካከል የሆነው ኖቫ ኮኔክሽንስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በእለቱ የ5 ኪሎ ሜትር የአዋቂዎች እና የአንድ ኪሎ ሜትር የህፃናት የጎዳና ላይ ውድድር መደረጉን አስታውቋል። ውድድሩን በሰሜን አሜሪካ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍፁም አረጋ እና አትሌት ኮረኔል ደራርቱ ቱሉ አስጀምረውታል። ከ20 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ታዋቂ አትሌቶች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ ከያኒያንን ጨምሮ አፍሪካዊያን ዲያስፖራዎች በክብር እንግድነት ተገኝተዋል። ውድድሩን በሴቶች ብርሃኔ አደሬ በመሪነት ያጠናቀቀች ሲሆን በወንዶች ደግሞ ግርማ ኢላላ ቀዳሚ ሆኗል። አሸናፊዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ነፃ የአየር ቲኬት በስጦታ ተበርክቶላቸዋል። አምባሳደር ፍፁም አረጋ ባደረጉት ንግግር የሩጫ ውድድሩ በዲሲ ከሚከበረው የኢትዮጵያ ቀን አንዱ መርሃግብር ነው ብለዋል። ዝግጅቱ ዲያስፖራዎች ለሚኖሩበት ማህበረሰብ እና ለመላው አፍሪካ ለሚያደርጉት አስተዋፆ ማሳያ ነው ሲሉም ገልፀዋል። የታላቁ የአፍሪካ ሩጫ ውድድር ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አበዛ በበኩላቸው፤ የዚህ ውድድር መዘጋጀት የአፍሪካ ዲያስፖራዎችን እርስ በእርስ ለማቀራረብ ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል። ዲያስፖራውን የሚያቀራርቡ መሰል ክንውኖች በቀጣይነትም እንደሚዘጋጁ ነው አምባሳደር ፍፁም የገለፁት። በዲሲ በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ቀደም ብሎ ለአርቲስት ቴድሮስ ካሰሁን የአፍሪካ ህብረት የዲሲ ከተማ ለኪነጥበብ ላበረከተው አስተዋጾ እውቅና ሰጥቷል። ለአትሌት ደራርቱ ቱሉም እንዲሁ የሜሪላንድ ግዛት በአትሌቲክስ ዘርፍ ላበረከተችው አስተዋፆ እውቅና ሰጥቷታል። የሩጫ ውድድሩ የተዘጋጀው  በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ ኖቫ ኮኔክሽንስ በተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅትና በዋሽንግተን ዲሲ የከንቲባ ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ትብብር ነው። ታላቅ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ በየአመቱ የሚካሄድ ብዙሃኑን የሚያሳትፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም