ለህዝቦች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንሰራለን---አዲሱ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር

54
ሐምሌ 15/2011 የአማራ ክልላዊ መንግስት የነበሩ ችግሮች በመፍታት ለክልሉና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ህዝቦች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አዲሱ ተሿሚ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስጌን ጥሩነህ ገለጹ። ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ከተሾሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ነው ይህንን የገለጹት። በዚህ ወቅት እንዳሉት  በኃላፊነት ዘመናቸው ትኩረት ሰጥተው ከሚሰሯቸው መካከል የህዝቦች ፍትሃዊ  ተጠቃሚነትና የህግ የበላይነትን ማስከበር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተፈጠረው የፖለቲካ ብልሽት ምክንያት የህዝቦች እርስ በርስ ግንኙነት ሻክሮ መቆየቱን ገልጸው በተለይም የአማራ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች እንዲገለልና በጥላቻ እንዲታይ በተሰራው ስራ እስከ ህይወት መስዋትነት የሚያደርስ እንግልትና መከራ እንደደረሰበት አውስተዋል። "የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ስለሚኮራ በየትኛውመ አካባቢ የሚኖር ህዝብ ነው "ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ሆኖም በሚኖርበት አካባቢ ሰርቶ የመኖር መብቱ እየተነፈገ መገፋቱን ተናግረዋል። ይሄ ደግሞ ባለፉት ዓመታት የተሰበከ የፖለቲካ ትርከት ያስከተለው ችግር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት ሁኔታው ተስተካክሎ የክልሉ ህዝቦችም ሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። " በተለይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የተፈጠረውን  ለውጥ ለመቀልበስ የሚደረግን የተንኮል ሴራ የአማራ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ከመላ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ይታገለዋል" ብለዋል። ክልሉን የግጭት  ቀጠና ለማድረግ ታቅዶበት እየተሰራ ቢሆንም በትግስትና በኢትዮጵያዊነት ስሜት እንጂ በስሜት ተገፋፍቶ ወደ አላስፈላጊ እርምጃ መሄድ ጉዳት እንጂ ትርፍ እንደሌላው  አቶ ተመስጌን ገልጸዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ህዝብ የሚያነሳቸው የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን ጨምሮ በርካታ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በተጠናና በሰላማዊ መንገድ የሚመለሱ ናቸው። "ህዝብን ህዝብ ጠልቶት አያውቅም "ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ የአማራን ህዝብ በሌሎች  እንዲጠላ ያደረጉት የተወሰኑ ቡድኖች እንጂ ህዝብን በጠላትነት የሚፈርጅ መንግስትም ሆነ ህዝብ እንደሌለ አመልክተዋል። የነበሩ የተበላሹ የፖለቲካ ችግሮችን ለማስተካከል ፣ ሀገራዊና ክልላዊ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። "የክልሉ መንግስት እንደ ሀገር በፍቅርና በትብብር የሚሰራና የክልሉን ሰላም የማይሹ  ከምንጊዜውም በላይ ነቅቶ ይጠብቃል " ብለዋል። "በዋዛ ፈዛዛ የሚባክን ጊዜና እውቀት የለም "ያሉት አቶ ተመስጌን ይልቁንም ሀገራዊ ግንባታን በሚያጠናክርና የክልሉን ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በመፈታት ረገድ አቅምን አሟጦ የመጠቀም ስራ እንደሚከናወን  አብራርተዋል። የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በሚያደርገው ቆይታ የ2011 ዓ.ም የክልሉ የአስፈፃሚ አካላት የ11 ወራት ክንውን ሪፖርት ላይ ይወያያል። የክልሉን ዋና ኦዲተርና የጠቅላይ ፍርድ ቤት መስሪያ ቤቶችን ሪፖርትም የሚያዳምጥ ሲሆን የክልሉን የ2012 ዓ.ም በጀትና ሌላም ሹመት  እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም