በቦሌ ለሚና በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች 20 ሺህ ችግኞች ተተከሉ

221

አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2011 ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከ15 ተጠሪ ተቋማቱ የተውጣጡ አራት ሺህ የሚሆኑ ሠራተኞች በቦሌ ለሚና በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዛሬ 20 ሺህ ችግኞችን ተክለዋል።

የተተከሉት ችግኞች ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞች የሚያስከትሉትን ተፅዕኖ ለመቀነስና የስነ-ምህዳር ሚዛን ለማስጠበቅ ያግዛሉ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የተመረጡት የአካባቢውን ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ሚዛን በማስጠበቅ የተቋቋሙበትን ተልዕኮና ራዕይ እንዲያሳኩ ታስቦ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ገልጸዋል።

የችግኞቹ በፓርኮቹ መተከል የአገሪቱ የኢንዱስትሪ እድገት አቅጣጫ የአረንጓዴ ልማት መርሐ-ግብሩን ተከትሎ እንዲሄድ  መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነም ተናግረዋል።

መስሪያ ቤታቸው ባለፈው ዓመትም በፓርኮቹ ግቢ ችግኞች መትከሉን አስታውሰው ሌሎች ተቋማትም  ችግኞችን ሲተክሉ ተልዕኳቸውን ማሳካት በሚያስችላቸው መልኩ እንዲያደርጉት ጠይቀዋል።

የፓርኮቹ ከእንስሳት ንክኪና ተጽዕኖ የተጠበቁ መሆን፣ ፓርኩን የሚያስተዳድረው አካል በቅርበት መገኘት እንዲሁም የሚኒስቴሩ ክትትል ችግኞቹን ለመንከባከብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

መስሪያ ቤታቸው የዛሬ ሳምንት በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር በየረር ጃርሶ ወረዳ ወርጦ በተባለ ቦታ 50 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

የሚኒስቴሩ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ አቶ አዋሽ ይርጋ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር የሚስማማና የአፈሩን አይነት ተቋቁሞ መጽደቅ የሚችል የችግኝ ዝርያ ተመርጦ መተከሉን ገልጸዋል።

ይህም ችግኞቹ ሲጸድቁ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ እንደ ሚቴን፣ ካርቦን፣ ናይትረስ ኦክሳይዶችና ሌሎች መርዘኛ ጋዞችን በመሳብ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖ ለማመጣጠን ያግዛል ብለዋል።

የችግኝ ተከላው ተሳታፊ አቶ ፍቃዱ አሰፋም ችግኞች ለክትትልና ቁጥጥር በማይመቹ ቦታዎች መተከል የለባቸውም ይላሉ።

ችግኞች በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በእምነት፣ በትምህርት ተቋማትና በመሰል በሃላፊነት በሚጠበቁ አካባቢዎች ሲተከሉ ለእንክብካቤ ምቹ አጋጣሚ ስለሚፈጠር የመጽደቅ ደረጃቸው ከፍ እንደሚልም ተናግረዋል።