የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር 70 ሺህ ቶን ማዳበሪያ ወደ አገር ቤት አጓጓዘ

163

አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2011 የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ለመኸር የግብርና ስራ የሚውል 70 ሺህ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደብ ወደ አገር ቤት ማስገባቱን አስታወቀ።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በጂቡቲ ወደቦች የሚገኙ ገቢ ሸቀጦችን በፍጥነትና በቅልጥፍና ወደአገር የማስገባት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከሰበታ እስከ ጂቡቲ ወደቦች ድረስ የሚዘልቀው የባቡር መስመር የጭነትና መንገደኞች የማጓጓዝ ተግባር ማከናወን ከጀመረ አንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ አስቆጥሯል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ከታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የመንገደኞችና የጭነት ማጓጓዝ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የፕላኒንግ ኃላፊ አቶ አሜኑ ጁሃር እንደተናገሩት፤ ለወሳኝ ሸቀጦች ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ ነው።

አክሲዮን ማህበሩ ለዘንድሮ የመኸር ወቅት ግብርና ስራ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

እስካሁን ድረስም 70 ሺህ ቶን የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ በ26 የባቡር ጉዞ አዳማና ሞጆ ደርሶ ለግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ማስረከብ መቻሉን ተናግረዋል።

አክሲዮን ማህበሩ የሚያጋጉዘው በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አሚኑ፤ አክሲዮን ማህበሩ በገባው ውል መሰረት በፍጥነት አጓጉዞ ለተፈለገለት ዓላማ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

በበርካታ መኪና ተጓጉዞ በሶስት ቀናት ውስጥ የሚገባውን ሸቀጥ ከ10 እስከ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ከጂቡቲ ወደቦች ሞጆ ደረቅ ወደብ በባቡር የማድረስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ቢያንስ 75 ከባድ ተሽከርካሪዎች ከነተሳቢያቸው በሶስት ቀናት ውስጥ የሚያጓጉዙትን ጭነት በአንድ ቀን አንድ ባቡር ብቻ መጓጓዝ መቻሉ በተለይም ለነዳጅና የመኪና ዕቃ መለዋወጫ የሚወጣውን ወጪ የሚያቃልል አስተዋጽኦ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የሚሰጠው የማጓጓዝ አገልግሎት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት አቶ አሚኑ፤ በጫኝና አውራጅ የስራ መስክ ለተደራጁ 300 ያህል ሰዎች የስራ ዕድል ሊፈጥር መቻሉን ገልጸዋል።

አክሲዮን ማህበሩ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የትራንስፖርት ውል በመግባት የጭነት መጓጓዝ ስራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በተለይም በአስቸኳይ ወደአገር መግባት ያለባቸውን ሸቀጦች በተቀላጠፈ መንገድ እያጓጓዘ መሆኑን አቶ አሚኑ አስረድተዋል።

ወደስራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር ውል በመግባት ከፍተኛ ጭነት ወደአገር ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል።

የወጪ ንግድ ምርትን በቅናሽ ዋጋ በማጓጓዝ የወጪ ንግዱን ለማበረታታት የሚያስችል ተግባር እየተፈጸመ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት በ12 ዓይነት ካርጎዎች የተለያዩ የጭነት አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን ጥራጥሬ፣ ከሰል፣ ብረታ ብረት፣ ስኳር፣ ማዳበሪያ፣ ጋዝ፣ ኮንቴይነር፣ ትንንሽ መኪና፣ ጥጥ፣ ቡና፣ የቁም እንስሳት፣ እና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን የማጓጓዝ አቅም ያለው ነው።