የኢሉአባቦር ዞን ሴቶች በአገር አቀፍ ደረጃ በተያዘው ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል አሉ

80
መቱ ኢዜአ  ሐምሌ 15 /2011  በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘው መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን የኢሉአባቦር ዞን ሴቶች ገለጹ። በዞኑ በሚካሄደው መርሐ ግብር በአንድ ቀን 14 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ የዞኑ ቡና እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በዞኑ የመቱና የዶረኒ ወረዳዎች አንዳንድ ሴቶች ለኢዜአ እንደገለጹት ሴቶችንና ወጣቶችን በማስተባበር በመርሐ ግብሩ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ ተሰናድተዋል። የመቱ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት አወቀ እንዳሉ በአገር ደረጃ የተያዘው እቅድ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሴቶችን አነቃቅቷል። ''እንደ ግሌ በምኖርበት አካባቢ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች አዘጋጅቻለሁ''ብለዋል። ''በመርሐ ግብሩ ከኅብረተሰቡ ጋር ከምተክለው በተጨማሪ ለራሴ የምተክለውን ችግኝ ገዝቼ አዘጋጅቻለሁ'' ሲሉም አክለዋል። የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑ ሴቶች በክረምት ችግኝ ተከላው በንቃት ለመሳተፍ እያነቃቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ በክረምት ችግኝ ተከላው በንቃት እንዲሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ያስተላለፉት መልዕክት ከአካባቢ ጥበቃ ልማቱ ባለፈ በልማቱ የኅብረተሰቡን  ተሳትፎ እንደሚያሳድገው የተናገሩት ደግሞ የዶረኒ ወረዳ ኤሌሞ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ብርሃኔ ኃይሉ ናቸው። ''ሴቶችም በአደረጃጀቶቻቸው፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በንቃት በመሳተፍ ለእቅዱ ስኬት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል'' ብለዋል። የዞኑ ሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጽጌ ረጋሳ በበኩላቸው በተለይ ሴቶችና ወጣቶች ከክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ጋር የችግኝ ተከላውን በማቀናጀት ኅብረተሰቡን ማነቃቃትና አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። የዞኑ ቡና እርሻና ተፈጥሮሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የደን ልማት ባለሙያ አቶ መልካሙ ተሾመ የመቱ ከተማን ጨምሮ  በዞኑ 13 ወረዳዎች ሐምሌ 22 ቀን 14 ሚሊዮን የሚሆኑ የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በተከላው የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችና ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በኢሉአባቦር ዞን 90 ሚሊዮን የሚሆኑ የዛፍ ችግኞችን በ7ሺ 357 ሄክታር በላይ መሬት ላይ እየተተከሉ ነው። በተከላውም በ13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ100ሺህ በላይ ሕዝብ  በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ባለሙያው አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም