ኮሌራን መቆጣጠር ላይ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

71
ሀምሌ 15/2011 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ 986 የኮሌራ በሽታ ተጠቂዎች መመዝገባቸው ተነግሯል። አብዛኞቹ የበሽታው ተጠቂዎች በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች ነው የሚገኙት። እ.አ.አ 2030 ኮሌራን ከዓለም ላይ ለማጥፋት ያለመው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ነገ በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ ይካሄዳል። ኮሌራ በብዙ አዳጊ አገሮች ቀዳሚ የህብረተሰብ ጤና ችግር ሲሆን በተለይ ክረምትን ተከትሎ የሚከሰት መሆኑ መከላከሉን አዳጋች ያደርገዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታው በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ያደረገው የመከላከል ስራ የሞት ምጣኔውን መቀነስ ያስቻለ ነው። በሽታውን በዘላቂነት ለመከላከል የተከሰተባቸውን አካባቢዎችና ተጠቂ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ቦታዎችን በመለየት ክትባት የማዳረስ ስራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ኮሌራን እ.ኤ.አ በ2030 ከዓለም ላይ ለማጥፋት ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀ ሲሆን በዚህም የበሽታው መንስኤ ናቸው የተባሉትን የአየር ጸባይ ለውጥ፣ የህዝብ ብዛትና የከተሞች መስፋፋት ታሳቢ ተደርጎ ይተገበራል። ፍኖተ ካርታው በ20 አገራት የሚተገበር ሲሆን በተጠቀሰው ዓመት የበሽታውን ሰርጭት በ90 በመቶ ለማስወገድ ያለመ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በግንቦት 2010 ዓ.ም ባካሄደው 71ኛ መደበኛ ስብሰባው እ.አ.አ በ2030 ኮሌራን ከዓለም ላይ ለማጥፋት ድንጋጌ ማውጣቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስትም በተጠቀሰው ዓመት ኮሌራን ለማስወገድ ብሄራዊ የኮሌራ ማስወገጃ እቅድ በማውጣት ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል። የኮሌራ በሽታ በተበከለ ውሃና ምግብ የሚመጣ ሲሆን በቶሎ ወደ ህክምና መሄድ ከተቻለ በሽታውን ማስወገድ ይቻላል። ለዚህ ግን በቂ ስትራቴጂ፣ ትግበራ፣ ውጤታማ የቁጥጥር ስርዓት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም