ሚዛናዊው ተራራ

168
ጥላሁን አያሌው (ሚዛን ኢዜአ ) 1936ዓ.ም ፊትአውራሪ ዓለማየሁ ፍላቴ ከጎሬ ተነስተው ማሻ፤ቴፒና ሸኮን አቆራርጠው ፤ ግዙፎቹን በቆና ጋቸብ ወንዞችን በሀረግ ተሻግረው ከረጅም የቀናት ጉዞ በኋላ አንድ ከፍታማ ቦታ ላይ ደረሱ፡፡ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ትዕዛዝ አካባቢውን ለማስተዳደር የተላኩት ፊትአውራሪ ዓለማየሁም በሠራዊታቸው ታጅበው ከዚህ የተራራ ማማ ላይ ሆነው ዙሪያ ገባውን ይቃኙ ጀመር፡፡ ጉብታማው መልከዓ ምድርም ታች ታቹ ለልማት የሚውል ምቹ  የላዩ ከፍታደገሞ  ከጠላት ጥቃት የሚታደግ ደጀን ሆነላቸው ። ተራራው ግራ ቀኙን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሆኖም አገኙት፡፡ ይህኔ ፊት አውራሪ አለማአየሁ ዓለሙን እንዳየ ሰው በእጅጉ ደስ አላቸው ። አካባቢው ሚዛናዊ ሆኖ ስላገኙትም ”ሚዛን” ብየዋለሁ ሲሉ ይሰይሙታል፡፡ የተራራው ሚዛናዊነት ሁሉን እኩል የሚያሳይ ከመሆኑ የተነሳም ሚዛን ተባለ ፡ የኃላም ኃላም የንጉሡን ቅድመ ንግስና ስም በማከል ተራራውና ዙሪያው ” ሚዛን ተፈሪ ”ተሰኘ፡፡ የንጉሡ ዓላማ እንዲሰምር ተልዕኳቸውም ይሳካ ዘንድ ፊትአውራሪ አለማአየሁ ይታትሩ ጀመሩ ። ቀድሞ ወደህሊናቸው የመጣውም የትምህርት ነገር ነበር፡፡ ዕውቀት እንዲስፋፋ ፣ ዜጋ እንዲሰለጥንና ሀገር እንድትዘምንም ወዲያውኑ በ1936 ዓ.ም የቀለም ቤት አቋቋሙ፡፡ በፊትአውራሪ አለማየሁ ትጋትም የሚዛን ቁጥር አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዛሬ 75 ዓመት ተመሰረተ፡፡ ተማሪ ቤቱ የመጀመሪያ ተማሪዎቹን በደሳሳ የሳር ጎጆ ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ፡የቀለም አባት መምህራንም እንዲሟሉለት ተደረገ፡፡ የመጀመሪያ የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረውም በአምስት መምህራንና በአንድ ብርቱ ጥበቃ ነበር፡፡ በ1936ዓ.ም በሳር ጎጆ ሥራውን የጀመረው ትምህርት ቤቱ በ1945 ዓ.ም ወደቆርቆሮ ቤት ያደገ ሲሆን 157 ተማሪዎችን ተቀብሎ እስከ 4ኛ ክፍል ማስተማር ቻለ፡፡ እንደአጋጣሚ ዕድለኛ ሆንኩኝና የዚህን ታሪካዊ ባለውለታ ትምህርት ቤት 75ኛው ዓመት የአልማዝ እዩቤልልዩ በዓል ለመታደም በትምህርት ቤቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ተገኝቻለሁ፡፡ በእያንዳንዳችን የሕይወት ማህደር ውስጥ የትምህርት ቤት ትውስታችን ትልቁን ግማድ ይይዛል፡፡የተማሪ ቤት ትውስታ በብዝኃኑ እንቦቀቅላ አዕምሮ ላይ ላይለቁ ተለስነዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በነበረኝ ቆይታም ለአፍታ ወደ ልጅነት ትዝታዬ አንደረድሮኛል፡፡ ሰንደቅዓላማ ለመስቀል የሚደረግ እሽቅድምድም፤ከሰልፍ መኸል ድምጽን ከፍ አድርጎ መዘመር፤ደወል እንደተሰማ የሚኖር ሩጫ፤የክፍል አለቃ ቁጥጥር፤የዕረፍት ሰዓት ልፊያና ግፊያ፤አንዲት የጨርቅ ኳስን መጫወቱ የትምህርት ቤት ደማቅና አይረሴ አውዶች ናቸው ። የተለያየ ቀለማት ያላቸው አበባዎች፤ በየግድግዳው የተከተቡ ፅሁፎች ፤የወዳደቁ ወረቀቶች፤የተሰባበሩ ዴስኮች፤ክፍታ ክፍት መስኮቶች፤ያልተጸዳ መማሪያ ክፍል፤የመጽሐፍ ሽፋን ግንጣይ፤የተሞነጫጨረ ሰሌዳ፤ደቃቅዬ ጠመኔዎች ታዩኝ ። ብቻ የትየለሌ ሌላም ሌላም የትምህርት ቤታችን ትውኖች እዚህም ገጥመውኛል፡ያለፈ የሕይወት ገጼን እንዲገልጥም እድል ሰጥቶኛል፡፡ በዚህ የኃሊዮሽ ፍሰት መሀል ለመሀልም አንድ የተለየ ነገር እንድታዘብና እንዳብሰለስል አደረገኝ ፡፡ በሩን ተራምጄ ሁለትና ሦስት ህንጻዎችን ካለፍኩ በኋላ የትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች ጉራማይሌያዊነት ታወሰኝ፡፡ በቅርብ ዓመታት(ምንአልባትም ከአምስት አመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ) የተሰሩ በርካታ ዳስ አዳራሽ መሰል ቆርቆሮ ቤቶች አሉ፡፡ በአንጻሩ የትምህርት ቤቱ የመጀመሪዎቹ ብረት ለበስ ቤቶች ተከበው ብቻቸውን መኸል ላይ አሉ፡፡በከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ በሕዝብ ሀብትና በመንግስት በጀት በቅርብ በተሰሩት ቤቶችና 50 ዓመት ዕድሜ ባስቆጠሩ ቤቶች መካከል ያለው ልዩነት ትዕንግርታዊ ነው፡፡ አዳዲሶቹ ቤቶች ሚዛናቸውን የሳቱና የተንጋዱ፤ውሀ ልካቸውን ያልጠበቁ፤ምርጊታቸው የተላላጠ፤በሲሚንቶ ተሰሩ የተባሉ የመማሪያ ክፍሎች የተፈረፈሩና ለአገልግሎት ያልተመቹ ናቸው ። የሚገርመው ግን እነዚህ ቤቶች ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸዋል ፡ በህዝብ ተሳትፎ ፤ በመንግስት አቅም፤በግለሰቦችና ተቋማት ልገሳና ድጋፍ በሌላም ሌላም ጥረት የቆሙ ናቸው ፡፡ ብዙ የተወራላቸውና ብዙ የተተረፈባቸው ናቸው ።ትርፉ ግን …… ልብ ያለው ልብ የሚለው ይሆናል ። ምናልባትም እንደዚህ ባሉ ድኩማን መማሪያ ቤቶች የተማረ፤በተሰባበረ ወንበሮቻቸው የተቀመጠ ኢትዮጵያዊ ተማሪ፤በእዝነ ህሊናው  ተጽዕኖውን መገመት አያዳግተውም፡፡እንዲህ ባለ መልኩ የትምህርት ጥራትን   ለማምጣት መከጀልም ተላላነት ነው ፡፡ በሌላ ወገን 50 እና ከዚያ በላይ ዓመታትን ያገለገሉቱ ሁለት መማሪያ ክፍሎች ደግሞ ከላይ በተጠቀሱት ለአቅመ ቤትነት ባልደረሱ ቤቶች ተከበው ይታያሉ ፡፡ እነዚህ ጥንታዊ ቤቶች ውሀ ልካቸውን እንደጠበቁ ሳይነቃነቁ ዘልቀዋል ።አሠራራቸውም ድንቅ ነው፡፡ የግድግዳቸው ቅርጽ፤ጥንካሬና ውበት፤የመማሪያ ክፍሎቹ መጠን ምቹነት፤ውበትና ጥንካሬ ሥነ ሕንጻዊ ሥሪታቸው ከአድናቆት ብዛት የጉድ ነው ያስብላል ፡፡ ጉዱን በGood የተኩ ናቸው ። ከቁሳዊ ወደ ሰብአዊ ሀብት እንሸጋገርና በ1950ዎቹ የነበረውን የተማሪና መምህር ጉድኝት፤ቅርርብና ክብብሮሽ የተመለከተ አንድ አብነት እናንሳ ፡፡ በ1950ዓ.ም የትምህርት ቤቱ ተማሪ የነበሩት አቶ አለማየሁ ገብረጻድቅ አንድ ቀን የአባታቸውን በቅሎ እየሳቡ ወደ ጠጅ ቤት ይሄዳሉ ፡፡ የያኔው ተማሪ አለማየሁ በቅሎዋን እደጅ አስሮ ከአባቱ ጉያ ተሸጉጦ እየጠጣ ነው፡፡ የትምህርት ቤት መምህሩም ድንገት ወደ ጠጅ ቤቱ ገቡ ፡ ፡የጠጅ ቤቱ እድምተኛ በነቂስ ከተቀመጠበት ተነስቶ የአክብሮት አቀባበል አደረገላቸው፡፡ መምህሩ ለተበረከተላቸው አክብሮት አፀፌታውን በመመለስ በተዘጋጀላቸው የክብር ወንበር ላይ ሊቀመጡ ሲሉ የክፍል ተማሪያቸውን ከጎን ያያሉ ፡፡ ይህኔ መምህሩ እንደመቆጣት እየቃጣቸው "ግራአዝማች ልጁን ጠጅ እያጠጣኸው ነው"ብለውአቶ ገብረጻድቅን ይጠይቋቸዋል፡፡ አቶ ገብረጻድቅ አክብሮት ባልተለየው ሁኔታ "ኧረ ብርዝ ነው መምህር የሚጠጣው"  ሲሉ ይመልሱላቸዋል፡፡ መምህሩ የተማሪያቸውን ነገር አሳስቧቸውና አላስችል ቢላቸው "እስኪ ልቅመሰዋ" ብለው ሊያረጋግጡ ሲከጅሉ፤አቶ ገብረጻድቅ  "መምህር የልጅ አይቀመስም" ቢሉዋቸው ጊዜ እድምተኛው በሞላ ተሳሳቀ፡፡ ለመምህር የሚሰጥ አክብሮት የላቀ ነበር ።መምህርም ለተማሪው የልጁን ያክል ይጨነቅ ነበር ። ከዚህ በራቀ ደግሞ የሀገር አደራን ፣ ትውልድ ቀረጻን፤ሙያዊ ኃላፊነትን መወጣትን፣  ከዛሬ ነገን ማማተርንና አርቆ አሳቢነትን  የሚስተዋልበት ነበር ፡፡ በአልማዝ እዮቤልዩ በዓሉ ላይ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች፤የከተማው ነዋሪዎች፤የዞንና የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች በበዓል አከባበር ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ታዳሚዎቹም ባለውለታ ትምህርት ቤታቸውን በትዝታ እየጎበኙ ሁለትዮሽ ስሜት ይታይባቸው ነበር፡፡ አንድም ታሪክ ታሪክ ነውና ትዝታም ትዝታ በመሆኑ ሁሉም ሲያልፍ ዞረው ሲያዩት ያምራል እንዲሉ ከትውስታ ምንጫቸው እየጨለፉ መጠጣቱን ተያይዘውታል፡፡ በአንጻሩ የ75 ዓመት አዛውንት አንጋፋ ትምህርት ቤታቸው ደረጃው ባለመሻሻሉና እድገት ባለማሳየቱ የውለታ ቁጭት፤የኃላፊነት ፀፀት ፈጥሮባቸዋል፡፡ እናም ያለፈ የሄደውን እያወሱ ስለመጪው ቀጣዩ እየሰነቁ ይመክሩ ጀመር ። ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ይገንቡ፤ጊቢው መዋብ አለበት የሚሉና ሌላም ሌላም ለትምህርት ቤቱ ዕድሜና ደረጃ  የሚመጥን ግንባታ ስለሚሰራበት ሁኔታ ውይይት አካሄዷል ፡፡ በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት አበበ አቅራቢነት በቀጣይ ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ትንትን ተግባራት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ አቶ ሀብተማርያም ካዝንቴት 1959 ዓ.ም የትምህርት ቤቱ የስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው ብቸኛ ትምህርት ቤት እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሀብተማርያም እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ለታላላቅ ቁምነገር ያበቃ አንጋፋ ትምህርት ቤት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ በእኛ ጊዜ ያኔ 1959ዓም ትምህርት በቅርበት ማግኘት አስቸጋሪ በነበረበት ወቅት እንድንማር ከማስቻሉም ባለፈ ሁሉንም ልጆቼን በትምህርት ቤቱ አስተምሬበታለሁ ። ለቁም ነገርም አብቅቻለሁ ብለዋል፡፡ በቀሰሙት የቀለም ትምህርት ከ1965 ዓ.ም  ጀምሮ በትግራይ፣ ጅማ፣  ካፋ ፣ቤንቺ ማጂና በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በሃላፊነት ሰርተዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ታሪካዊ ቢሆንም አሁን ያለበት ሁኔታ ግን ትኩረት እንዲሰጠው ያስገድዳልም ብለዋል፡፡ ለማስፋፊያውም በግላቸው የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውንና ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ ነውና ህብረትና ትብብር ካለ ትምህርት ቤቱን ማሻሻል ይቻላል ያሉት ደግሞ ቄስ ቀለመወርቅ ጥበቡ ናው፡፡ ከተማው ካለው የሕዝብ ቁጥርና ትምህርት ቤቱ ካለበት ጫና አንጻር የማስተናገድ አቅሙን ማሳደግ እንደሚገባና ዕድሜውን የሚመጥን ማስፋፊያ እንደሚያስፈልገው ቄስ ቀለመወርቅ ተናረዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት ሚፍታህ ደሊ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ የቤተ ሙከራ ግብዓትና የመማሪያ ክፍል ዕጥረት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ 2ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምር ቢሆንም ትምርት ቤቱ ካለው የግብዓት አቅርቦት አንጻር ግን ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከተማ መኸል በምቹ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የራሱ ገቢ የሚያመነጭበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላልም ብለዋል፡፡ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት አበበ እንዳሉት ትምህርት ቤቱ መሠረታዊ የመማር ማስተማር ችግሮቹን የሚፈታ የማስፋፊያ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ቤተ መጻሕፍት፤ቤተ ሙከራ፤ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ፤የመማሪያ ክፍል፤መዝናኛን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ግንባታዎችን ያሟላ የማስፋፊያ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡ አጠቃላይ የማስፋፊያ ግንባታውም ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅም አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ፤የግልና የመንግስት ተቋማት፤የዞንና የከተማ መስተዳደር አካላት እነዲሁም ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች በሚገኝ ድጋፍ የሚሰራ ይሆልም ብለዋል፡፡ ኮሚቴ ተዋቅሮ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ ይገባል ያሉት አቶ ታምራት ትምህርት ቤቱን ደረጃውን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም