የሕግ የበላይነትን ማስፈንና የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች መፍታት ለነገ የማንለው ተግባር ነው - የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር

69
ሀምሌ 15 /2011 የሕግ የበላይነትን ማስፈንና የክልሉን ህዝብ ጥያቄዎች መፍታት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን አዲሱ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ተናገሩ። ርዕሰ መስተዳድሩ ሹመታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር በተለይ ከክልሉ ህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ቅድሚያ ሰጥተው ለመመለስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። "እንደ ወንድም ተበዳደሩ እንደ ባዕድ ተቆጣጠሩ" ሲሉ የአበው ምሳሌ የጠቀሱት አቶ ተመስገን ከሚፈለገው ግብ  ለመድረስ እንደ ወንድም አብሮ መስራትና የአካባቢን ሠላም መጠበቅ የግድ እንደሚልም መልዕክት አስተላልፈዋል። "በክልሉ የሚነሱ የማንነትና የድንበር ጥያቄዎች ለግጭት መንስኤ መሆን የለባቸውም" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ "ህጋዊ በሆነ መንገድ እንደምንፈታቸው ላረጋግጥ እወዳለሁ" ሲሉም ተናግረዋል። የክልሉ ህዝብ ለአገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተዋጽኦ ያደረገና ታሪካዊ አሻራ የጣለ መሆኑን ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ የሴራ ፖለቲከኞች በክልሉ ህገወጥ እንቅስቃሴ እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም ማናቸውንም ችግሮች በሰከነ መንገድ በማየት በህጋዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል "በአብሮነትና በመተሳሰብ ልንሰራ ይገባል" ብለዋል። "የክልሉ ህዝብ ከሌሎች የአገሪቱ ዜጎች ጋር በአብሮነት እስከሰራ ድረስ ምንም አይነት ፈተና ቢመጣ የማንወጣው ነገር የለም" ሲሉም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይልና የበርካታ ተፈጥሯዊ ሃብቶች ባለቤት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በአግባቡ በመጠቀም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማረጋገጥ እንሰራለንም ብለዋል። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በንግግራቸው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና የክልሉን እድገት ለማስቀጠል ግብርናን ማዘመንና ኢንቨስትመነትን ማበረታታት የግድ እንደሚል አውስተዋል። ለዚህም በክልሉ የተጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአፋጣኝ እንዲጠናቀቁና ሌሎች የኢንቨስትመነት አማራጮች እንዲሰፉ ከማድረግ ባለፈ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመንገድና ሌሎች የክልሉ ጥያቄዎች እንዲመሰሉ 'ጥብቅ ክትትል ይደረጋል' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም