አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሆኑ

234
አዲስ አበባ ሀምሌ 15/2011አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተመረጡ። የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው። ምክር ቤቱ የአቶ ተመስገንን ሹመት በሙሉ ጽምጽ ማጽደቁን ተከትሎ እርሳቸውም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቸና ከተማ የተወለዱት አቶ ተመስጌን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮምፒዩተር ሳይንስና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በለውጥ አመራርና አስተዳደር ተቀብለዋል። አቶ ተመስገን ቀደም ሲል በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ ዋና መምሪያ፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና በሌሎች ክልላዊና ፌዴራላዊ የመንግስት ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። ከክልል እስከ ወረዳ በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ያገለገሉት ተሿሚ፣ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እስከተሰየሙበት ጊዜ ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትር የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በዚህ ወቅት የክልሉን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አስታውቀዋል። በአገርና በክልሉ እየተንጸባረቁ ያሉትን ችግሮች ለማስተካከል ከሌሎች ክልሎችና ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። የአማራ ሕዝብ በተበዳይነት ስሜት እየቆዘመ የልማት ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል ያሉት አቶ ተመስጌን፣ ይህንን በማስተካከልና ወቅቱን ያገናዘበና ክልላዊና አገራዊ እድገት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ሕዝብ ያነሳቸው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ወደ ግጭት የሚከቱ ሳይሆን፣በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ጉባዔው እስከ ፊታችን ሐሙስ ድረስ እንደሚቀጥል ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም