በኦሮሚያ ክልል ለ“አረንጓዴ አሻራ ቀን” የችግኝ ተከላ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ተናገሩ

121

ሀምሌ 14/2011 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በመጪው ኃምሌ 22 ቀን 2011 ዓም ለሚካሄደው የ“አረንጓዴ አሻራ ቀን” ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ የቪዥን ብራይት በጎ አድራጎት ማህበር ጋር  በመተባበር በዱከም ከተማ አካባቢ ያለውን አነስተኛ የደን ሽፋን ለመመለስ ‘ዱከም መልካ’ በሚባል ስፍራ ዛሬ ተገኝተው  ከማህበሩ አባላት ጋር ችግኝ ተክለዋል።

የማህበሩ አባላት ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር የሚስማሙ እስከ 20 ሺህ የሚገመት ችግኝ ነው ዛሬ የተከሉት።

በዚሁ ወቅትም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር የኦሮሚያ ክልል በመላው አገሪቱ ለመትከል በእቅድ ከተያዘው ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ውስጥ ግማሹን ለመሸፈን እየሠራ ነው።

በተለይም በመጪው ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓም ለሚካሄደው የ“አረንጓዴ አሻራ ቀን” የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ትግበራ ክልሉ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀዋል።

በእለቱ በመላው አገሪቱ ሊተከል በእቅድ የተያዘው 200 ሚሊዮን ችግኝ ሲሆን የኦሮሚያ ግን 250 ሚሊዮን ችግኝ በክልሉ ብቻ በመትከል ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ነው ምክትል  ፕሬዚዳንቱ የጠቆሙት።

ለዚህም በጂ.ፒ.ኤስ በመታገዝ ችግኝ የሚተከልበት ቦታና ጉድጓድ ከመሰናዳቱም በላይ አስፈላጊው የሰው ኃይልም መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

መላው የክልሉ ህዝብ በእለቱ በነቂስ ወጥቶ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በመሳተፍ ታሪክ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ ዛፍ፣ አቮካዶ፣ ቡናን ጨምሮ እስካሁን 870 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ ችግኞች በመተከል ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

አነስተኛ የደን ሽፋን ለመመለስ ወደ ዱከም ከተማን መርጠናል ያሉት የቪዥን ኢትዮጵያ ምክትል ቦድር ሰብሳቢ አቶ አዲሱ ደበላ ህብረተሰቡ ችግኝ መትከል ያለበት የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ወደነበረበት ለመመለስ እንጂ ተከልኩ ለማለት መሆን እንዳሌለበትም አሳስበዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ለተከላቸው ችግኞች ዘላቂነት አስፈላጊውን ክብካቤ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።

የማህበሩ ዋና እስኪያጅ በበኩላቸው አነስተኛ የደን ሽፋን ለመመለስ በማህበሩ ስም ችግኝ ሲተክሉ ዱከም ከተማን በሁለተኛነት መምረጣቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከግማሽ በላይ የማህበሩ አባላት ወደ ተከላው ከማምራታቸው በፊት በትራፊክ አደጋና በወሊድ ምክንያት ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚሆን ደም መለገሳቸውም ታውቋል።

ማህበሩ በበጎ አድራጎት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ አግኝቶ መንቀሳቀስ በጀመረ በስድስት ወር ውስጥ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንና በጽዳትና ሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎ ማድረጉንም አክለዋል። ።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት በመላው የኢትዮጵያ ገጠር 3 ነጥብ 88 ቢሊዮን፤ በከተማ ደግሞ 760 ሚሊዮን በአጠቃላይ 4 ነጥብ 41 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉ ይታወቃል።

ለችግኝ ተከላው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል።

ተራራማ መልክዓ ምድር የበዛባት ኢትዮጵያ የቀድሞ ደን ሽፋኗ የተመናመነና አፈሯ እየታጠበ በመሆኑ የደን ሽፋኗን ለመመለስ፣ የዝናብ ስርጭቱን ለማስተካከል፣ የሙቀት ሁኔታውን ለማሻሻል የደን ሽፋን ሁኔታ መለወጥ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት አገራዊ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ወጥቶ እየተሰራ ይገኛል።