የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ሊካሄድ ነው

303

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ሐምሌ 14 /2011ዓ.ም የተለያዩ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የሚሳተፉበት “የአዲስ ወግ” ውይይት መድረክ ነገ በድሬዳዋ እንደሚካሄድ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የጽህፈት ቤቱ የፕሬስ ሰክሬተሪያት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ማምሻውን ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት አዲስ ወግ በሚል የሚኪያሄደው ውይይት በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለማጠናከር ያግዛል፡፡

መድረኩ በሀገር ዕድገትና ልማት ጉዳይ አዳዲስ አስተሳሰቦችና ሙሁራን ወደፊት እንዲደመጡ ከማድረግ በተጨማሪ በሀገር መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የጎላ ጠቀሜታ ስላለው ለሁለተኛ ጊዜ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ንጉሱ ገለፃ የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚስተናገዱበትና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት “አዲስ ወግ-አንድ ጉዳይ” በሚል የተጀመረው የውይይት መድረክ የሃሳብ ነጻነት በስፋት የሚገለፅበትና የሚስተናግድበት በመሆኑ ለሀገር መንግስት ግንባታ ይጠቅማል ፡፡

“አዲስ አበባ ከተኪያሄደው የአዲስ ወግ በመቀጠል በድሬዳዋ ነገ የሚኪያሄደው ውይይት ኢትዮጵያ ስትገነባ የተጓዝንባቸው ሂደቶች ይፈተሻሉ” ብለዋል፡፡

በዚህ ሂደት የተስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ መለየት በቀጣይ ሀገር በመገንባት ሂደት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው አቶ ንጉሱ የገለፁት፡፡

እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ በሀገር ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በውይይት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር መቻል ለሀገር ግንባታ ቁልፍና መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ስለ ሀገረ- መንግስት ግንባታና ስለብሔራዊ መግባባት ነገ በድሬዳዋ የሚደረገውን ውይይት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ የድሬዳዋ አስተዳደርና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ማዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡

በውይይት ላይ የሶማሌ፣ የሐረሪና የአፋር ክልሎች፣ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የምስራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች እንዲሁም ከፌደራልና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሙሁራን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡