የህዝብ ለህዝብ መድረኩ የተዘራውን የውሸት ትርክት ለማረም እንጂ ለፖለቲካ ትርፍ አይደለም...አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

80
ባህር ዳር (ኢዜአ) ሐምሌ14 / 2011  “የሶማሌና የአማራ ክልል የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረክ የተዘጋጀው የአማራ ህዝብ በሶማሌ ክልል ህዝብ ላይ ከፍተኛ ብዝበዛ እንዳደረገ ተደርጎ ባለፉት ዓመታት የተዘራውን የውሸት ትርክት ለማረም እንጂ ለፖለቲካ ትርፍ አይደለም “ ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ተናገሩ። የሶማሌ እና የአማራ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል። በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ  እንደገለጹት የሶማሌ ክልል መንግስትና ህዝብ ከአማራ ክልል ህዝብና መንግስት ጋር ውይይት ለማድረግ በባህር ዳር ከተማ የተገኘው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አይደለም። “ይልቁንም የአማራ ህዝብ ላለፉት ዓመታት በጨቋኝነትና በዝባዢነት ተመድቦ በውሸት ስለተተረከና በተለይ የሶማሌ ህዝብ ላይ የከፋ በደል እንዳደረሰ ተደርጎ ስለተሰበከ ነው” ብለዋል ። በዚህ ምክንያት የሶማሌ ክልል ህዝብ የአማራ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች በተለየ በጥላቻ ሲመለከተው መቆየቱን አቶ ሙስጠፌ አመልክተዋል። ይህ የተሳሳተ ትርክት ውሸት መሆኑ ስለታመነበት የሶማሌ ክልል መንግስት የተለያዩ የህብረተስብ ክፍሎችን የወከለ ልዑክ ይዞ ወደ ባህር ዳር ከተማ እንዲመጣና ከወንድም የአማራ ህዝብ ጋር ተቀራርቦ እንዲመክር መደረጉን ተናግረዋል። “የተጠናከረች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ኢትዮጵያዊያን በአንድ ላይ ሊቆሙ እንጂ ሊነጣጠሉ አይገባም” ብለዋል ። የሶማሌ ክልል መንግስትና ህዝብ የውሸት ትርክቶችን በማረም ለሀገር አንድነት መጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር የተጠናከረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማድረጉን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። “ወቅቱ የብሔር ፖለቲካ ከመቼም በላይ የተጋጋለበት ወቅት በመሆኑ ሀገሪቷን ለአደጋ እንድትጋለጥ አድርጓታል” ያሉት ደግሞ የአማራ ዴሞክራዊያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው ናቸው። እንደእሳቸው ገለጻ የኢትዮጵያን አንድነት የማይሹ ጽንፈኞች ህዝቡን በፈለጉት መልኩ እየነዱ ከጎናቸው ለማሰለፍ እየጣሩና ያልተሰለፈውን ለማጥፋት ያለ የሌለ አቅማቸውን እየተጠቀሙ ይገኛሉ። “ሀገር በብሔር ፖለቲካ ተከፋፍላ ለአዳጋ ስትዳረግ ለሀገራዊ አንድነትና ለህዝቦች እኩልነት የሚቆም መሪ ያስፈልጋታል” ሲሉም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ አንድነቷን የሚያስጠብቅ መሪ የምትሽበት ወቅት ላይ መሆኗንም አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል ። የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳደር በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያና ለህዝቧቿ አንድነት የሚጠቅም ሀሳብ እያራመዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። የሁሉም ክልል መሪዎች ክልላቸውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደሚመራ መሪ በማሰብ የኢትዮጵያ አንድነት ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል። ላለፉት ሦስት ቀናት በባህር ዳር ከተማ ቆይታ ያደረገው የሶማሌ ክልል ልዑክ በጣና ሐይቅ የሚገኙ የታሪክ መስዕቦችን የጎበኘ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የህዝብ ለህዝብ ውይይቱን አድርጎ ቆይታውን አጠናቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም