የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ከመንግስት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ሲቪክ ማህበራት ገለጹ

57
ጎንደር ኢዜአ ሐምሌ 14/2011 የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለመጠበቅ ከመንግስት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ በጎንደር ከተማ የሚንቀሰቃሱ ሲቪክ ማህበራት ገለጹ።፡ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሄዷል። ውይይቱን ያዘጋጀው የጎንደር ሰላምና ልማት ሸንጎ ሰብሳቢ አቶ ባዩ ፈረደ እንዳሉት ሲቪክ ማህበራት የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ኃላፊነት ወስደው መስራት አለባቸው። ሸንጎው ሲመሰረት መንግስትና ህዝብን ድልድይ ሆኖ በማገናኘት የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና የህዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ዓላማ በማድረግ በአካባቢው በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ከመንግስት ጎን ሆኖ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ከከተማዋ አልፎ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት የህዝብ ለህዝብ ግንነኙነቶችን በማድረግ ወደ ነበረበት ሰላም እንዲመለስ የጎላ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል፡፡ ለውጡን ተከትሎ የመጡ መልካም እንቅስቃሴዎችን እንዲቀጥሉና የተበላሹ አካሄዶች እንዲስተካከሉ በማድረግ ከመንግስትና ሌሎች አደረጃጀቶች ጋር በመሆን መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሸንጎው በቀጣይ ከሁሉም በከተማዋና በአካባቢዋ የሚንቀሳቀሱ ማህበራትና አደረጃጀቶች ጋር በጋራ በመሆን የከተማዋ ልማት እንዲፋጠን  የሚደግፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከግዮን አማራ በጎ አድራጎት ማህበር የመጡት አቶ ዘመነ ሀብቱ በበኩላቸው  “ እያንዳንዱ ማህበር የተቋቋመበት ዓላማ ቢኖረውም የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ግን ከመንግስት ጎን ሆኖ በአንድነት መስራት አለበት “ ብለዋል፡፡ ወጣቱ ከስሜት በመውጣት ለዴሞክራሲና ሰላም መስፈን መስራት እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ ከቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማህበር አባል ሻምበል ዳኘው መኮንን ናቸው፡፡ በተለይም ፀጥታ አካሉ የአካባቢውን ህዝብ በማስተባበር የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ የሲቪክ ማህበራቱ የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ለመጠበቅ ከመንግስት ጋር በመተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ አማረ የአካባቢውን ህዝብ ለመጥቀም ከተደራጁ ማህበራት ጋር ለመስራት ድርጅቱ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በህጋዊ ማህበራት ጀርባ ሆነው ሌላ አጀንዳ የሚያራምዱ ግለሰቦችን ግን መነጠል እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡ ህዝብን በሚጠቅም ስራ ለሚንቀሳቀሱ ማህበራት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በሪሁን ካሳሁን ናቸው፡፡ ማህበራት ከተደራጁበት ዓላማ ጎን ለጎን ህግና ስርዓት ለማስከበር መደገፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማህበራት፣ የሙያ ማህበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት አባቶችና የመንግስት አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም