የሰላም ችግሮችን በመደማመጥና በውይይት መፍታት ይገባል– ምሁራን

224

ባህር ዳር ኢዜአ ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም -በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ የሰላም ችግሮችን በመመካከርና በውይይት መፍታት እንደሚገባ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ ።
ዩኒቨርሲቲው ትላንት 9 ሺህ 750 ተማሪዎችን ባስመረቀበት ስነ ስርአት ላይ ምሁራኑ በሀገሪቱ የሰላም ችግሮችና መንስኤዎች ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሶሻል ሳይንስ ትምህርት ክፍል የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ቃለወንጌል ምናለ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገሪቱ እየታየ ያለው የሰላም ችግር በለውጥ ወቅት የሚጠበቅ ነው ።

በተለይም የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች በመደማመጥና በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ሀገሪቱ እንደ ሀገር አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል ።

“የፖለቲካ ልሂቃንና አመራሩ የኢትዮጵያን የዜጎችን ፍላጎት መሰረት ባደረጉ ጉዳዮችና መፍትሄዎች ላይ አተኩረው በጋራ በመወያየት መስራት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል ።

ተመራቂ ተማሪዎችም ወደ ስራ ዓለም በሚቀላቀሉበት ወቅት የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ በሚቀጥልበትና የህዝቦች አንድነት በሚረጋገጥበት ሁኔታ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መክረዋል።

ምሁራንም ችሮችን ለይተው መፍትሄ ማመላከት የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ የራሳቸውን አስተዋፆ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አመላክተዋል ።

እንደ ዶክተር ቃለወንጌል ገለጻ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ህዝቡ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በጋራ የሚመክሩባቸው መድረኮች በመንግስት በኩል ሊመቻቹ ይገባል ።

“የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ ሳይኖረውም መኖር የሚችል፤ የመቻቻል ባህልና እሴት ያለው ህዝብ ነው” ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው በአደጋ መከላከልና ስጋት ቅነሳ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገድፍ ናቸው።

“በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት ብዝሃ የሆንን ህዝቦች በክልል መካለላችን ጌጥ እንጂ እርስ በእርሳችን ሊያከፋፍለንና ሊያጋድለን አይገባም” ብለዋል።

ምሩቃንም ከጎጥ አመለካከት በመራቅ በተማሩባቸው መስኮች ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ማገልገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል ።

“በሀገርም ሆነ በውጭ የሚገኙ አንዳንድ ምሁራን ከፖለቲካ የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን በመገንዘብ ሀገርን የሚያፈርስ መልእክት ከማስተላለፍ ሊቆጠቡ ይገባል “ ሲሉም መክረዋል ።

ምሁራን የተዛባን ታሪክ በማስተካከል የተለያየን ህብረተሰብ አንድ ሊያደርግ የሚችል ስራ በመስራት የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ አመላክተዋል።

“ፖለቲከኞችም ከእርስ በእርስ ትርምስ ወጥተው የህብረተሰቡን ፍላጎትና የሀገሪቱን ዕድገት መሰረት ያደረገ የሃሳብ ፍጭትና ክርክር በማድረግ በሀገሪቱ አንድነት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳረፍ መስራት አለባቸው” ብለዋል።

በሂውማንቲ ፋኩልቲ የእንግሊዘኛ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዘውዱ እምሩ በበኩላቸው በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተለያዩ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት በሚፈልጉ ኃይሎች እየተሰራጩ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎች ለሰላም አጦት ምክንያት በመሆናቸው ዜጎች መረጃዎችን ሳያጣሩ መቀበል እንደሌለባቸውም መክረዋል ።

“ተመራቂ ተማሪዎችም እንደተማረ ኃይል የሚለቀቁ መረጃዎችን መዝኖ ማየት ይጠበቅባቸዋል” ያሉት ዶክተር ዘውዱ ምሁራን ማህበራዊ መስተጋብሮችን የሚያጠናክሩ መረጃዎችን በመስጠትና ምርምሮችን በመስራት አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ አመላክተዋል ።

“በምርምርና በህይወት ተሞክሯችን የምናገኛቸውን ዕውቀቶች መሰረት በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የምናሸጋግራት ኢትዮጵያ ምን መምሰል እንዳለባት በማስተማር የሀገርን አንድነት መጠበቅ ይገባናል” ሲሉም ዶክተር ዘውዱ መልዕክት አስተላልፈዋል ።