የኢትዮጵያና የአሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ልምምድና ስልጠና ተልዕኮን በተሻለ ብቃት ለመፈፀም የሚረዳ መሆኑ ተጠቆመ

105

ድሬዳዋ ሐምሌ14 /2011 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከአሜሪካ ወታደሮቸ ጋር በመሆን እያካሔደ ያለው ልምምድና ስልጠና የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በበለጠ ብቃት ለመወጣት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር ገለፀ።
የዩኤስ አሜሪካና የኢትዮጵያ ሠራዊት በሁርሶ ‹የኮንቲጀንት› ሠራዊት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የጋራ ወታደራዊ ስልጠና በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ሳምንት በተጀመረው ስልጠና ላይ የተገኙት በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ተወካይ ብርጋዴር ጀኔራል ሀብታሙ ጥላሁን እንደገለፁት በሰላም ማስከበር አለም አቀፍ ተልዕኮ ሂደት ያሉ ልምዶችንና የእርስ በእርስ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እየተካሔደ ያለው ስልጠና ሽብርተኝነትን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ ነው ።

ወታደራዊ ስልጠናው የቡድን መንፈስ በማጎልበት ሀገራዊ ተልኮ በብቃት ለመወጣት የሚረዳ መሆኑንም ብርጋዴር ጀኔራሉ ተናግረዋል ፡፡

“በተጨማሪም ሰራዊቱ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ሂደት እያሰመዘገበ የሚገኘውን ውጤት ለማሳደግም ስልጠናው ወሳኝ ነው” ብለዋል።

በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል ክላውተር ጂር በበኩላቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀኔራሎች ላይ በተፈፀመው ግድያ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው ለኢትዮጵያ ህዝብና ለመከላከያ ሠራዊት አባላት መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

በሁርሶ ከተጀመረው የጋራ ስልጠና በተጨማሪ በህክምናና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰላም ማስከበር ሠራዊትን ብቃት የተሟላ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“በሶማሌና በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር በጋራ መሰልጠኑ ለቀጣይ ተልዕኮ ያግዛል” ብለዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ተቀናጅተው በጋራ ለመስራትና ያላቸውን ጥምረት ለማጠናከር ስልጠናው ወሳኝ መሆኑንም ጀነራል ክላውተር ገልፀዋል፡፡

በሰላም ማስከበር ማዕከል የሎጂስቲክ መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው “ስልጠናውና የልምድ ልውውጡ ሁሉንም እንደ የስራ ድርሻውና ኃላፊነቱ የሚያቧድን መሆኑ ለቀጣይ ሥራ በርካታ ልምዶች ለመለዋወጥ ያስችላል” ብለዋል፡፡

በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲጀንት ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ሚልኬሳ ረጋሳ እንደገለፁት ከትምህርት ቤቱ ሰልጥነው የወጡ የሰራዊቱ አባላት በዳርፋር፣ በአብዬ፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተግባር ተሰማርተው በአለም አቀፍ ደረጃ መልካም ዝናና ክብር ማትረፋቸውን ገልፃዋል፡፡

“አሁን እየተካሔደ ያለው የጋራ ስልጠና ደግሞ ዓለም አቀፍ ልምድ ካካበተ አገር ጋር በጋራ የሚካሄድ በመሆኑ የተሻለ ዕውቀት የሚቀሰምበትና ተልዕኮን የበለጠ በብቃት ለመወጣት የሚያስችል ነው” ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ለማሳካትም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል ሲል የሀገር መከላከያ ሠራዊት የላከውን መግለጫ  ነው ፡፡