በስራው ዓለም ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ አራማጆችን ለመከላከል ጠንክረው እንደሚሰሩ ምሩቃን ተናገሩ

84

ባህር ዳር ሐምሌ 14 / 2011 ወደሥራ ሲሰማሩ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ ከማከናወን ባለፈ ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ አራማጆችን ለመከላከል ጠንክረው እንደሚሰሩ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂዎች እንደገለጹት በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በብሔር ፖለቲካ ምክንያት መገፋፋትና አለመቻቻል እየሰፋ በተቃራኒው የኢትዮጵያዊያን ልዩ መገለጫ የነበሩት መከባበርና መደማመጥ እየጠፉ መጥተዋል፡፡

ይህን ለማስተካከልና የህዝቡን የቀደመ የመከባበርና የአንድነት ባህል ወደ ቀድሞው ለመመለስ ከአዲሱ ትውልድ በተለይም ከዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

ከምሩቃን ተማሪዎች መካከል በቴክስታይል ኢንጂነሪንግ የተመረቀው አንዳርጌ ጌታቸው እንዳለው አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን ያቆዩት የተለያየ ብሔርና ቋንቋ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በጋራ መስዋትነት ከፍለው ነው፡፡

ዛሬ ሰዎች ሀገርን አስቀድመው ሳይሆን በየብሔራቸው ጉያ ተደብቀው እንዲያስቡ የሚያደርጉ አካላት ለብሄራቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ አሰበው ሳይሆን ከራሳቸው የግል ፍላጎት አንጻር ብቻ እያሰቡ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የቀደምት አባቶች ብሔርና ቋንቋ ሳይገድባቸው ያቆዩዋትን ሀገር ትክክለኛ ታሪክንና እውነታውን ብቻ በመመርመር ሀገራዊ አንድነትን የሚያዳብር ተግባር ለማከናወን መዘጋጀቱንም ተመራቂው አስታውቋል፡፡

“እንደ ሀገር የተደቀነውን የአደጋ ስጋት ለመመለሰ በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀን የምንወጣ ወጣቶች ትልቅ ኃላፊነት አለብን” ያለው ደግሞ የህብረተሰብ ሳይንስ ተመራቂ ተማሪ ቁምላቸው በቀለ ነው፡፡

ምሩቃን ወደአካባቢያቸው ሲመለሱ የጽንፈኛ ፖለቲከኞችን ዓላማ ሳያውቁ የሚያራምዱ ወገኖችን እውነታውን በማስተማር ወደመልካም ተግባር መመለስ እንደሚገባም ተናግሯል።

በተለይ ወጣቱ ከኢትዮጵያዊ አንድነት የበለጠ አማራጭ አለመኖሩን ተረድቶ የአክራሪ ፖለቲከኞች ሰለባ ከመሆን እራሱን ሊጠብቅ ይገባል ሲልም ገልጿል፡፡

“የኢትዮጵያን የቀደመ ማንነት ለመመለስ የቀደሙ አባቶች ምን አይነት የጋራ ታሪክ ነበራቸው የሚለውን ቀድሞ ማወቅ ያስፈልጋል” ስትል የገለጸቸው ደግሞ የመካኒካል ምህንድስና ተመራቂዋ ተማሪ የሺመቤት ሰለሞን ናት፡፡

የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ የጥቂት ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ አራማጆችን ሀሳብ በእንጭጩ መቅጨት እንዳለባቸውም ተናግራለች፡፡

“መመረቅ ብቸውን መብቃት ሳይሆን በተማሩት ልክ ሃገርንና ህዝብን ከችግር ማውጣትና ለቀጣይ ሀገራዊ ጉዞ በጋራ በመምከር መፍትሄ ማበጀት ነው” ያለችው ወጣቷ እሷም ለእዚህ መዘጋጀቷን ገልጻለች።

በቀጣይ በምትሰማረበት የሥራ መስክ ኢትዮጵያ ከገጠማት ወቅታዊ ችግር እንድትወጣ በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻዋን እንደምትወጣም አስታውቃለች፡፡

ምሩቃንተማሪዎችወደህብረተሰቡሲመለሱለህብረተሰቡየሀገሪቱንነባራዊሁኔታናለኢትዮጵያየሚጠቅመውንበማስገንዘብየድርሻቸውንእንዲወጡምጠይቃላች።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት መርሀግብሮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 9 ሺህ 750 ተማሪዎች ትናንት ማስመረቁ ይታወሳል።