አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት በዳይመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር አሸነፈ

75
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 14/2011 አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት በእንግሊዝ ርዕሰ መዲና ለንደን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር አሸናፊ ሆኗል። ለሁለት ቀናት በለንደን ስታዲየም የሚካሄደው የ2019 10ኛ ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ትናንት በአንደኛ ቀን ውሎው የተለያዩ ውድድሮች ተካሄደዋል። በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት 13 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ ከ86 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ነው ያሸነፈው። አትሌት ሐጎስ ከኖርዌያዊው አትሌት ጃኮብ ኢንብሪግስተን ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው የውድድሩ የመጨረሻ 250 ሜትሮች ላይ ፍጥነት በመጨመር ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቋል። አትሌት ሐጎስ ከኖርዌያዊው አትሌት ከባድ ፉክክር ገጥሞት እንደነበር የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ-ገጹ አስፍሯል። አትሌት ሐጎስ ከሁለት ሳምንት በፊት በስዊዘርላንድ ሉዛን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር ክስተት በኋላ ትናንት እልህ አስጨራሽ ፉክክር ገጥሞት ማሸነፍ ችሏል። በሉዛን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ አምስት ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ሐጎስ ሩጫው አንድ ዙር እየቀረውና የመጨረሻው ዙር ደወል እየተደወለ ባለበት ሁኔታ አሸንፌያለሁ ብሎ ደስታውን እየገለፀ ሳለ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከኋላው ቀድሞት በመግባት አሸናፊ የሆነበት አጋጣሚ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ውድድር አትሌት ሐጎስ የቀረውን 400 ሜትር ጨርሶ አስረኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን አትሌቱ ካለው ልምድ አንጻር የሰራው ስህተት ያልተለመደና እንግዳ ነገር እንደሆነ የስፖርቱ ቤተሰቦች ሲገልጹም ነበር። ''በስታዲየሙ የነበሩ ደጋፊዎች ከፍተኛ የድጋፍ ድምጽ ሲሰጡኝ የውድድሩ አሸናፊ የሆንኩ መስሎኝ ነው ደስታዬን ስገልጽ የነበረው'' ሲል ከውድድሩ በኋላ አትሌት ሐጎስ በሰጠው ቃል ገልጿል። ትናንት በተካሄደው የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ጃኮብ ኢንብሪግስተን 13 ደቂቃ ከ2 ሴኮንድ ከሶስት ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ ኬንያዊው አትሌት ኒኮላስ ኪሜሊ 13 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። የዚህኛው ዙር የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር የዳይመንድ ሊግ ነጥብ አያሰጥም። ትናንት በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች በተካሄደው ውድድር እንግሊዛዊቷ አትሌት ላውራ ሙር፣ ኬንያዊቷ አትሌት ዊኒ ቺቤት እና ካናዳዊቷ አትሌት ጋብሪዬላ ስታፎርድ በቅደም ተከትል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በውድድሩ የተሳተፈችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አክሱማዊት አምባዬ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። በለንደን ስታዲየም የሚካሄደው የ2019 10ኛ ዙር የዳይመንድ ሊግ ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎው የተለያዩ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች አትሌት ለተሰንበት ግደይ ትሳተፋለች። በውድድሩ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው ሲፋን ሀሰን የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት አግኝታለች። ትናንት በለንደን ስታዲየም የተጀመረው የ10ኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ዛሬም ሲቀጥል የአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች ጨምሮ የዳይመንድ ሊግ ነጥብ የሚያሰጡ የተለያዩ የአትሌቲክስና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ይካሄዳሉ። 11ኛ ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በእንግሊዝ በርሚንግሀም ከተማ ይካሄዳል። በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ 14 ከተሞች የሚካሄደው ዳይመንድ ሊግ ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም በቤልጂየም ርዕሰ መዲና ብራሰልስ በሚካሄደው ውድድር ይጠናቀቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም