የባለኃብቶችን የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያግዝ የሩጫ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄደ

112

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ14/2011ባለኃብቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያግዝ ግንዛቤ መፍጠርን ያለመና “ለኢንዱስትሪ ልማት እንሩጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የሩጫ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄደ።
መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው በዚሁ የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች፣ ተወካዮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

የሩጫ ውድድሩን በመተባበር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ናቸው።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው እንደገለጹት የግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ተሳትፎ እንዲያድግ ግንዛቤ መፍጠር የውድድሩ ዓላማ ነው።

በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ባለኃብቶች ከኢንዱስትሪ ይልቅ በስፋት የተሰማሩት በንግድና አገልግሎት ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት ኢንጂኒየር መላኩ ባለኃብቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ዝቅተኛ ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

መንግስት ኢትዮጵያ ከግብርና ወደኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እንድትሸጋገር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ከመሆኑ አኳያ የግሉ ዘርፍም  በኢንዱስትሪ ልማት ያለውን ተሳትፎ   ማሳደግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

ባለኃብቶች በዘርፉ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ የማስተዋወቅ ስራ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሩጫው መዘጋጀቱን የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አመልክተዋል።

ባለኃብቱ ትኩረቱ ወደኢንዱስትሪው እንዲሳብ ከማድረግ አኳያ የማስተዋወቅ ተግባር ጠቃሚ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጂኒየር መላኩ  የማስተዋወቁ ስራ ውጤትና ስኬት የሚታየው ግን በአጭር ጊዜ ሳይሆን በረጅም ጊዜ ውስጥ እንደሆነም ነው ያስረዱት።

የግሉ ዘርፍ  የኢንዱስትሪ ልማት ተሳትፎ እንዲያድግ የተጀመሩት የቅስቀሳ ስራዎች ከሩጫ ባለፈ በሌሎች መርሃ ግብሮችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ በበኩላቸው የኢንዱስትሪው ልማት ለኢኮኖሚው ዘላቂ እድገት ወሳኝ መሆኑን የተገነዘበው መንግስት ስትራቴጂና ፖሊሲ በመቅረጽ ዘርፉ እንዲጎለብት የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2025 በአፍሪካ ተቀዳሚ የኢንዱስትሪ መዳረሻ እንድትሆን የተያዘው እቅድ እውን እንዲሆን የግሉ ዘርፍ ህብረተሰቡ እና ሌሎች አጋር አካላት አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በወንድ በግል የተወዳደረው ደረጀ ያይራድ አሸናፊ ሲሆን ስንታየሁ አጥላባቸው ከዋሪት እና እሸቱ ፈዬ በግል በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሴቶች በግል የተወዳደረችው የሮሳን አለማየሁ አንደኛ ስትወጣ፤ ብርቄ እጀታ ከጄጄ ቴክስታይል፣ ሀና ጉተማ ከሰንመን ጋርመንት በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ሰንሙን ጋርመንት አጠቃላይ የቡድን አሸናፊ ሲሆን ጄጄ ቴክስታይልና ዛምራ ኮንስትራክሽን ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያና በመስታወት የተቀረጸ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ውድድሩን ያጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ተሻለሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ለአሸናፊዎች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል።