ዛምቢያዎች በመንግስታቸው የሚታየውን ሙስና የሚቃወም ሰልፍ አደረጉ

126

ኢዜአ ሀምሌ14/2011ቢጫ የለበሱና ቢጫ ፖስተር የሚያውለበልቡ ዛምቢያውያን ሃገራቸውን እየጎዳ ያለውን ሙስና የሚያወግዝ ሰልፍ አድርገዋል፡፡

በትናትናው እለት በመዲናዋ ሉሳካ በተካሄደው ሰልፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የዜጎች ህይወት እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

ሰልፈኞቹ መንግስት የሃገሪቱን ገንዘብ ለድሆች እንዲያውል የጠየቁ ሲሆን የተሻለ ትምህርትና የጤና አገልግሎትም እንሻለን ብለዋል፤ በአንፃሩ ባለስልጣናትና አስፈፃሚዎች ብዙ ቤቶችን እና ገንዘብ ከመሰብሰብ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡

“የሃገሪቱ ገንዘብ በአግባቡ ከተዳደረ ህይወታችን ይሻሻላል፣በመሆኑም በየደረጃው ያሉ ዜጎች ህይወት እንዲሻሻልም እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡

ሰልፈኞቹ በያዙት ቢጫ ካርድ ለመንግስታቸው ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሰልፉ ነገሮች ከመባባሳቸው በፊት መንግስትን ለማስጠንቀቅ የወሰድነው እርምጃ ነው ያሉት ሰልፈኞቹ በሃገሪቱ የተንሰራፋው ሙስና ትውልድን የሚያጠፋና የልጆቻችንን እጣ ፈንታ የሚያበላሽ ነው ብለዋል፤መንግስትም በዚሁ አጋጣሚ ዛምቢያውያን የሚሉትን ያድምጥ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ኢድጋር ሉንጉ የአምባገነንነት አገዛዝን በማራመድ እንደሚተቹ የገለፀው የሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ እኤአ በጥር 2018 የፋይናንስ ሚኒስትራቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸውን አስታውሷል፡፡

በመንግሰት ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና በሃገሪቱ አመፅ እንዲስፋፋ እያደረገ መሆኑም በዘገባው ሰፍሯል፡፡