ድርጅቱ ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲና በሐረር ከተማ ለሚገኘው የአቦከር መሰናዶ ትምህርት ቤት ድጋፍ አደረገ

77
ሐረር  ሐምሌ 13 /2011- ስቲም ሲነርጂ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲና በሐረር ከተማ ለሚገኘው የአቦከር መሰናዶ ትምህርት ቤት ግምታቸው 10 ሚሊዮን ብር የሆኑ የኤሌክትሮኒክስ እና የአይቲ ቤተ መከራ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። ድጋፉ ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸውን ክህሎት ይበልጥ እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ጌታቸው ገዛከኝ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ድርጅቱ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግና የሒሳብ ትምህርቶች በተቀናጀ መንገድ እንዲሰጡ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በተንቀሳቀሰበት ዘጠኝ ዓመታት በ14 የተለያዩ ሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የኤሌክትሮኒክስና የአይቲ ቤተ ሙከራዎችን የማቋቋም ሥራ ማከናወኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም በሐረማያ ዩኒቨርሲቲና በሐረር ከተማ ለሚገኘው የአቦከር መሰናዶ ትምህርት ቤት ተጨማሪ ቤተ ሙከራዎችን ማቋቋሙን ገልጸው፣ በቀጣይም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወልደጻዲቅ በበኩላቸው “በአካባቢው የሚገኙት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በበቂ ሁኔታ የተደራጁ ቤተ ሙከራዎች ስለሌሏቸው የንድፈ ሐሳብ ትምህርቶችን በተግባር አስደግፈው ከመስጠት አንጻር ውስንነት ይታይባቸዋል” ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ይህን ችግር ለመቅረፍ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ተማሪዎችን በክረምት ወራት ወደ ተቋሙ በማምጣት የተግባር ትምህርቶችን እንዲቀስሙ ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ለአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በክረምት ወራት ሲሰጠው የነበረውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት እንዲጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። ስቲም ሲነርጂ ያደረገው ድጋፍ ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመዱ የሚያደርግ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ናቸው። ተማሪዎች ወደ አይሲቲ ማዕከል በመምጣት ክህሎታቸውን ሊያዳብሩ እንደሚገባ የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊው፣ ድርጅቱም ድጋፉን በሌሎች ትምህርት ቤቶችም እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዊተር ኢንጅነሪግ መምህር ወሂብ አቡበከር በበኩላቸው ተማሪዎች የኤሌክትሮኒክስና አይቲን በቤተ ሙከራ ቀድመው መጀመራቸው ለከፍተኛ ትምህርታቸው አጋዝ መሆኑን ተናግረዋል። የኮምፒውተር ማዕከል በተለይ ተማሪው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ቴክኖሎጂውን ተረድቶ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲመጣ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም “የመመረቂያ ጽሁፍና የምርምር ስራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅትም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቀድሞ ለመረዳት ያግዛል” ሲሉ ተናግረዋል። በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ የሚገኘው የሞዴል ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ በፀሎት ታደሰ በበኩሉ የሚሰጠው ትምህርት በቴክኖሎጂ መታገዙ የተማሪውን አቅም ያጎለብታል ብሏል። ተማሪዎች ወደከፍተኛ ትምህርት በሚገቡበት ወቅት ለአይሲቲ ትምህርት እንግዳ እንዳይሆኑ የማዕከላቱ መከፈት ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ተናግሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም