በአገር አቀፉ የችግኝ ተከላ ከሰባት ሺህ በላይ አባሎቼ ይሳተፋሉ - የአካል ጉዳተኞች ማህበር

100
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 14/2011 በመጪው ሀምሌ 22 ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ላይ ከሰባት ሺህ በላይ አባላቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበር አስታውቋል፡፡ የብሄራዊ ማህበሩ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ባህሩ ከሊል ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀምሌ 22 ቀን 2011ዓ.ም በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካል ጉዳተኞች የበኩላቸውን ድርሻ በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ባህሩ፤ አባላቱ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ  የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ሲሳተፉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አስተባባሪነት በእንጦጦ ተራራ አካባቢ በተዘጋጀላቸው ቦታዎች ችግኝ በመትከልና በየጊዜው ክትትል በማድረግ ለውጤት ማብቃታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በችግኝ ተከላ መርሃግብሩ እለት አንድ አባል ቢያንስ 20 ችግኝ እንዲተክል እቅድ መያዙን የጠቀሱት አቶ ባህሩ በዚህ ስሌትም በማህበሩ አባላት በእለቱ ከ140 ሺህ በላይ ችግኝ እንደሚተከል ጠቅሰዋል። ችግኝ መትከል ብቻ ስኬት አይደለም ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ችግኙ እንዲጸድቅ በቅርበት በመከታተል በኩል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል። በኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገብሬ ተሾመ በበኩላቸው የማህበሩ አባላት በተለያዩ ጊዜያት የችግኝ መትከላቸውን ነው የተናገሩት። የማህበሩ አባላት ከዚህ ቀደም በደብረ-ብርሃንና በደሴ አካባቢ ባሉት ቦታዎች ላይ በርካታ የችግኝ ተከላ ስራዎች ያከናወኑ ቢሆንም ተገቢው እንክብካቤ ባለመደረጉ የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱን  ጠቁመዋል። በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አስተባባሪነት በተካሄዱ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ በርካታ የማህበሩ አባላት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣታቸውንም ገልጸዋል። በመጪው ሀምሌ 22 በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ ለመሆን መዘጋጀታቸውንና ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን ለእንክብካቤውም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ገብሬ፤  በተለይ በየመንገዱ የሚተከሉ የዛፍ ችግኞች አይነ ስውራንን ታሳቢ  ያደረጉ መሆን እዳለበት ነው የጠቆሙት። በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሄራዊ ማህበር ያገኘናት ወጣት ራሄል ገሰሰ በበኩሏ በሀገር አቀፉ የችግኝ ተከላ መርሃግብር መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ  ተናግራለች። በማህበራቸው በኩል በተለያዩ ጊዜያት በችግኝ ተከላ ትሳተፍ እንደነበረ የተናገረችው ራሄል፤ ዘንድሮም በአገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከጓደኞቿ ና ከስራ ባልደረቦቿ ጋር ለመሳተፍ መዘጋጀቷንም ጠቅሳለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም