በኦሮሚያ 199 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለማምረት ርብርብ እየተደረገ ነው

49
አዳማ (ኢዜአ) ሐምሌ 13/2011 በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የመኽር አዝመራ በዋና ዋና ሰብሎች ከ199 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ገለጹ። አስተባባሪው ዶክተር ግርማ አመንቴ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ለ2011/12 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን ከ6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ለመሸፈን ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውናል ። በእስካሁኑ ሂደት ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው ከእቅዱ አፈፃፀም አንፃር ሲታይ ክንውኑ 50 በመቶ ላይ መድረሱን ገልጸዋል። "በዘር ከተሸፈነው 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ሚሊዮን የሚሆነው በኩታገጠምና በቴክኖሎጂ ታግዞ የተዘራ ነው" ያሉት ዶክተር ግርማ በዋናነት የሚለሙት ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍና ባቄላ መሆናቸውን ጠቁመዋል። እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ በበጀት ዓመቱ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያና ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ የሰብል ምርጥ ዘር የማቅረብ ስራ እየተከናወነ ነው። "እስከ አሁን ድረስም 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያና ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ ፣ ባቄላ፣ አተርና ሌሎች ሰብሎችን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት ተችሏል" ብለዋል ። በክልሉ ታርሶ የተዘጋጀውን መሬት እስከ መጪው ወር አጋማሽ ድረስ በዘር ለመሸፈን በቅንጅት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። አልፎ አልፎ የምርጥ ዘር እጥረትና ለአርሶአደሩ በወቅቱ አለመድረስ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው "አሁን የታየው የግብዓት አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ከክልል እስከ ቀበሌ በትብብር እየሰራን ነው" ብለዋል። በክልሉ ግብርና ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከተቋማዊ አደረጃጀት ጀምሮ የቴክኖሎጂና የግብአት፣ የገጠር ፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት፣ የገበያ ትስስር ፣ የመስኖ ፣ የመካናይዜሽን እንዲሁም የኤክስቴሽን አገልግሎትና የተፈጥሮ ሀብት ላይ በሙሉ አቅም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በበጀት ዓመቱ ለወጣቶችና ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ከ2 ሺህ በላይ የእርሻ ትራክተሮችን ለማቅረብ እየተሰራ ነው ተብሏል ። "በአርሲ ዞን የበሌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በቀለ ያዳቴ በሰጡት አስተያየት የእርሻ ማሳችንን ደጋግመን በማረስ ለዘር ዝግጁ አድርገን እየጠበቅን ነው" ብለዋል። የአርሲ ዞን ጮሌ ወረዳ ያኢ ጉጉ ቀበሌ  ነዋሪ አርሶ አደር ታዬ ጌታቸው  በበኩላቸው "የእርሻ ማሳችንን ደጋግመን በማረስ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን እየዘራን ነው" ሲሉ ተናግረዋል ።   እስከ አሁን ድረስ ስምንት ኩንታል ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በእጃቸው መግባቱን ጠቅሰው የባቄላ፣ አተርና ገብስ ምርጥ ዘር ተጠቅመው መዝራታቸውን ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም