የሰሊጥና ሩዝ ልማትን ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውን በትግራይ አርሶ አደሮች ተናገሩ

83
ሽሬእንዳስላሴ ኢዜአ ሓምሌ 13/2011 በተያዘው የመኸር ወቅት ሰሊጥና የሩዝ ሰብል ልማትን ለማጠናከር የተሻሻሉ የግብርና ግብአቶችን በመጠቀም እየሰሩ መሆናቸውን በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ። በዞኑ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በማሳተፍ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በሰሊጥ፣ለውዝና ሩዝን ለማልማት ተቅዷል። አርሶ አደር መብራህቶም ተስፋዬ በታህታይ አዲያቦ ወረዳ የገምሃሎ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በተያዘው የመኽር ወቅቱ ምርጥ የሰሊጥ ምርጥ ዘርን  በመጠቀም ባላቸው አንድ ሄክታር ማሳ ላይ እያለሙ መሆናቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል። ከዚህም  11 ኩንታል ምርት ይጠብቃሉ። "የሚያስፈልጉ የግብርና ግብአቶችን በመጠቀም ሰሊጥ የማምረት ልምድ እንዳላቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ፣ አምናም ካለሙት መሬት  ዘጠኝ ኩንታል መሰብሰብ እንደቻሉ አስታውሰዋል። ሌላው የዚሁ ግንባር ቀደም አርሶ አደር መብራህቶም ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው በመስመር መዝራትን ጨምሮ የተሻሻለ የግብርና ግብአቶችን በመጠቀም የሰሊጥ ልማት እያሄካዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። እያለሙ ያሉትም በአንድ ሄክታር ማሳቸው  ላይ ነው ለገበያ ተደራሽ ለመሆንና ከግብርና ባለሙያዎች የሙያ ድጋፍ በቀላሉ ለማግኘት ማሳቸው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታ ገጠም ተግተው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ባለፈው የመኸር ወቅት ለሩዝ ልማት ተስማሚ በሆነው አካባቢያቸው በአንድ ሄክታርማሳቸው አልምተው 25 ኩንታል ምርት እንደሰበሰቡ የተናገሩት ደግሞ የፀለምት ወረዳ  አርሶ አደር  ተስፋአለም ገብረመድህን ናቸው። በተያዘው የመኽር ወቅትም ‘’ኔሪካ 13’’ የተባለ ምርጥ የሩዝ ሰብል በመጠቀምና በመስመር በመዝራት የተሻለ ምርት ለማግኘት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። አርሶአደር በእምነት በላይ የተባሉት የዚሁ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው እንዳሉት ባለፈውዓመት  የመኸር ወቅት በሄክታር 27 ኩንታል የሩዝ ምርት አግኝተዋል። በአሁኑ ወቅትም ከማሳቸው ጋር የሚስማማ " ኔሪካ 4 " የተባለው ምርጥ  የሩዝ ምርት በመጠቀምና በመስመር በመዝራት በሄክታር 30 ኩንታል ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ ነው። የዞኑ  አስተዳዳሪ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ክብሮም ብስራት እንደገለጹት በዞኑ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በሰሊጥ፣ለውዝና ሩዝ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ ነው። ይህም በተያዘው የመኸር ወቅት በዞኑ ገበያ ተኮር ሰብሎችን በብዛትና በጥራት ለማምረት የያዘውን እቅድ አካል መሆኑን አመልክተዋል። ባለፈው ዓመት የመኽር ወቅት ሰሊጥ በአማካይ በሄክታር ስድስት ኩንታል የተገኘው ዘንድሮ  ወደ ሰባት ኩንታል ሩዝ ደግሞ ሄክታር ከ26 ወደ 28 ኩንታል ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በተያዘው የመኸር ወቅት በዞኑ  ሰሊጥ፣ለውዝና ሩዝን ጨምሮ ከ243 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር በመሸፈን ከስድስት ሚሊዮን 200ሺህ  ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም