የወራቤ ዩኒቨርስቲና የአካባቢው ማህበረሰብ በጋራ ችግኝ ተከሉ

120

ሆስዕና ኢዜአ ሐምሌ 13/2011 የወራቤ ዩኒቨርስቲና የአካባቢው ማህበረሰብ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የታቀደውን የአረንጓዴ አሻራ ቀን እንዲሳካ በመደገፍ ዛሬ በጋራ ችግኝ ተከሉ።

በችግኝ ተከላው የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አለሙ ስሜ “የተከልነውን ችግኝ በመንከባከብና ሀገራዊ ሰላምን በማስጠበቅ ለኑሮ ምቹና ተሰማሚ የሆነ ንፁህ አየር እንድንተነፍስ በማድረግ ሁላችንም የሚጠበቅብን ማድረግ አለብን” ብለዋል።

ችግኝ መትከል ለአየር ንብረት ለውጥና ለአፈር መሸርሸር መጠበቅ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ኢንጅነር ቶፊክ ጀማል ናቸው ።

ሁሉንም ያሳተፈ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ማካሄዱ ቅንጅታዊ ስራ ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳይና ሀገርን በጋራ መለወጥ እንደሚችል አመለካች እንደሆነም ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት መካከል አርሶ አደር ጀማል ሁልቀሮ እንዳሉት የአካባቢ ጥበቃ ስራ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ተጎድቶ የነበረው መሬታቸው ለም እየሆነ መምጣቱንና ምርታማነታቸው ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህ በመነሳሳት በአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው የመጀመሪያ  ዓመት የስፖርት ሳይንስ ተማሪ ወርቅነሽ በቀለ “የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የአካባቢው ጥበቃና በሀገር ሰላም ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይጠበቅብናል “ብላለች ።

ከሁሉም ተቻችሎ በመኖር ሀገሪቱ ከእሷ የምትጠብቀውን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

የወራቤ ዩኒቨርስቲና የአካባቢው ማህበረሰብ ዛሬ በጋራ የተከሉት ችግኝ ከአንድ ሺህ በላይ እንደሆነ ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።