የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ለፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ እውቅና ሰጠ

366

ሐምሌ 13/2011 የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ የገዳ ስርዓትን ለአለም ማህበረስብ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ እውቅና ሰጠ ።

ለፕሮፌሰር አስመሮም እውቅና የተሰጣቸው ዩኒቨርስቲው ለዘጠነኛ ጊዜ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 5 ሺህ 200 ተማሪዎችን ዛሬ በስመረቀበት ወቅት ነው።

ለፕሮፌሰር አስመሮም እውቅና የተሰጣቸው ዩኒቨርስቲው ዛሬ ተማሪዎችን በማስመረቀበት ስነ ስርዓት ወቅት ነው ።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ እንደገለፁት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት በቦረናና ጉጂ ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች በተለይም በአሬሮ ፣ ያቤሎና ሜጋ ወረዳዎች በመገኘት በገዳ ስርዓት አመጣጥና በኦሮሞ ህዝብ ባህል ላይ ጥናት በማድረግ ለአለም ያስተዋወቁ ናቸው።

“የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ህዝብ ለአለም ያበረከተው አኩሪ ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ዘይቤ መሆኑን በመፃፍ ለአለም ያስተዋወቁ ባለውለታችን ናቸው” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸው እውቅና የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ታሪክ ለአለም ህብረተሰብ በማስተዋወቅ የነበራችው ሚና ታሳቢ በማድረግና ለማመስገን ጭምር እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ፕሮፌሰር አስመሮም በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብ ማንነትን ከመጠበቅና አንድነቱን ጠብቆ ከማቆየት አንፃር የገዳ ስርዓት ሚና የላቀ እንደነበር ጠቅሰው ስርዓቱ ጥቁር ህዝቦች ለአለም ያበረከቱት ዲሞክራሲ መሆኑን ተናግረዋል።

የገዳስርዓት አስታራቂ ፣አቃፊና አብሮነትን ያስተማረ በመሆኑ ከምዕራቡ ዴሞክራሲ ጭምር የተሻለ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ “ምክንያቱ ደግሞ የገዳ ስርዓት ከህግ ባለፈ አለመግባባቶችን በድርድርና በማስታረቅ ጭምር የሚፈታ በመሆኑ ነው “ብለዋል ።

ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ በገዳ ስርዓት ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የፃፉት መፅሐፍ ህትመቱ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ በቅርቡ ተደራሽ እንደሚደረግ አመልክተዋል

የተሰጣቸውን እውቅናና ሽልማት የገዳ ስርዓትን አኩሪ እሴት እንዲጠበቅና ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንዲሰሩ የበለጠ ተነሳሽነት የፈጠረላቸው መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።

በክብር እንግድነት የተገኙት በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በምረቃው ስነሰርዓት ወቅት እንዳሉት የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለማሻሻልና በየደረጃው የመንግስት መዋቅራዊ አስተዳደር ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት መረባረብ ወሳኝ ነው ።

“ተቋሙ ከክልሉ የተሰጠውን ልዩ ተልዕኮ ይዞ ለውጡን ለማሳካት በሚወጡ ፖሊዎች፣ ስትራቴጂና አሰራሮች ላይ ውጤታማ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን ይጠበቅበታል “ብለዋል።

የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በዕውቀት የበቃ አስፈፃሚ ኃይል መገንባት ሲቻል በመሆኑ በህጎች ፣ አሰራሮችና ስትራቴጂዎች ላይ የሚታውን የማስፈፀም አቅም ውስንነት ችግር ለማቃለል የተመራቂዎች ሚና የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም ቀልጣፋና ጥራት ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ተመራቂዎቹ በቆይይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር መተርጎም እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ባለፉት ሃያ ዓመታት ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዲፕሎማና በዲግሪ ማስመረቁ ተገልጿል።

በትምህርታቸው ብልጫ ለመጡ ተመራቂዎች ሽልማት የተበረከተ ሲሆን የችግኝ ተከላም ተከናውኗል።