በክልሉ 61 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ ተፈቱ

62
አሶሳ ሐምሌ 13 /2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ61 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ መስጠቱን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዛሬ አስታወቀ። የዐቃቤ ሕጉ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታ ፈንታው እንደገለጹት ለታራሚዎቹ  ይቅርታ የተሰጣቸው የክልሉ የይቅርታ ቦርድ በየሩብ ዓመቱ አገልግሎቱን ለመስጠት በያዘው ዕቅድ መሠረት ነው፡፡ ይቅርታው የተሰጠው በአሶሳ፣ በካማሽና መተክል ዞኖች ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ የሕግ ታራሚዎች እንደሆነም ገልጸዋል። ታራሚዎቹ ከተፈረደባቸው እሥራት አንድ ሶስተኛውን ማጠናቀቃቸውን አስረድተዋል። ታራሚዎቹ ወደ ኅብረተሰቡ ቢቀላቀሉ ምርታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመታመኑ ይቅርታውን መሰጠቱን  አቶ ጌታ ገልጸዋል። ይቅርታው በአስገድዶ መድፈር፣ በሙስና፣ በአገር ክህደት፣ ጭካኔ የተሞላበት ግድያና ሌሎች የዜጎችንንና የአገር ጥቅምን የሚጻረሩ ከባድ ወንጀሎችን እንደማያካትት አስታውቀዋል። በክልሉ በ2011 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ለ224 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ መስጠቱ ታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም