በሚዛን አማን ከተማ የኢኮኖሚ ፎረምና የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ተካሄደ

58
ሚዛን ኢዜአ ሐምሌ 13 / 2011 በቤንች ሸኮ የሚዛን አማን ከተማ የኢኮኖሚ ፎረምና የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ትናንት ተካሄደ። በከተማዋ እየጨመረ የመጣውን የሕዝቡ የመልማት ፍላጎት በዘላቂነት እንዲፈታም ሁሉም የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት አሰፋ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የከተማዋን የመሠረተ ልማትና የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሰራ ነው። የሕዝቡን ልማት ፍላጎቶች ለማሟላት ነዋሪዎችን ፣ ባለሀብቶችንና ተቋማትን በማሳተፍ ይሰራል ብለዋል። የፎረሙ ዋና ዓላማ በከተማዋ የሚከናወኑትንና ያሏትን  የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስተዋወቅ ነው ብለዋል። በቴሌ ቶኑ ከኅብረተሰቡ የሚሰበሰበው ገቢም በከተማዋ የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማት ተቋማት አገልግሎት እንደሚሟሉበት አስረድተዋል። በከተማዋ የኢንቨሰትመንት እንቅሰቃሴ እየተስፋፋ ቢሆንም፤ ከተማዋ ካላት የኢኮኖሚ አቅም አንጻር በሚፈለገው ደረጃ አልለማችም ያሉት ደግሞ  የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዘማች በዛብህ ናቸው። ፎረሙ የከተማዋ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመለየትና በማስተዋወቅ ረገድ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸውን ገልጸዋል። ከተማዋ የኢንቨስትመንት አማራጮቿን እንድትጠቀም በትኩረት መስራት እንደሚያስችል ተናግረዋል። በተለይ በሆቴል አገልግሎትና በኢንዱስትሪ ልማት ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ መኖሩንም  ከንቲባው አስታውቀዋል። በመንግሥት በጀት ብቻ የልማት ጥያቄን ስለማይሟላ ነዋሪዎችን ማሳተፍ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የሚዛን አማን ከተማ ገቢ ማሰባሰቢያ አስተባባሪ  አቶ ጌታሁን ተክሌ ናቸው። በፎረሙ በተካሄደው የገቢ ማሰባበሲያ ዝግጅት ከተለያዩ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶችና ተቋማት ስድስት ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል። የሳላሽ ሆቴል ባለቤት አቶ አብርሃም አዘረፈኝ በሰጡት አስተያየት ለከተማዋ ልማት 100 ሺህ ብር ለመስጠት ቃል የገቡ ሲሆን፣በቀጣይም ድጋፋቸው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም