የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኤሌክትሪክ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ አይደለም

127
አዲስ አበባ ሰኔ 4/2010 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ ለሚፈጠሩ አደጋዎች ለሚቀርብለት ጥሪ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ። ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ በሚወስደው መንገድ በተለምዶ ሰሜን ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኤሌክትሪክ ገመድ ተሸካሚ ምሶሶ በመኪና ተገጭቶ በአካባቢው ስጋት ፈጥሮ እንደነበር ነዋሪዎች ገልፀዋል። ነዋሪዎቹ በስፍራው ለተገኘው የኢዜአ ሪፖርተር እንደገለፁት የተበጠሰው የኤሌክትሪክ ገመድ በሰው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስሪያ ቤት ጥሪ ቢያደርጉም ከአራት ሰዓት በላይ  ለሚሆን ጊዜ ምላሽ አላገኙም። የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሶሶው ከዚህ በፊት ግጭት እንደደረሰበትና እንዲቀየር ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል። በግጭት የተበጠሰው የኤሌክትሪክ ገመድ መንገደኞችን እንዳይጎዳ ሲጠብቁ ከነበሩ ፖሊሶች መካከል  ኮንስታብል ጥላዬ ታፈረ እንዳስረዱት ከአንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ አምስት ሰዓት ድረስ በጥበቃ ላይ እንዳሉ ይናገራል። ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች በመገናኛም ሆነ በመኪና ቢሯቸው ድረስ በመሄድ ጥሪ ቢደረግላቸውም እንዳልተገኙ ነው የሚገልፁት። ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የችግሩን መንስኤ ኢዜአ ላቀረበው ጥያቄ   በሰጡት  ምላሽ የጥሪ ማዕከሉ በመጨናነቁ ጥሪዎችን ለመቀበል መቸገራቸውን እና ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ አደጋዎች በመብዛታቸው  ሰራተኞች በወቅቱ ሊደርሱ እንዳልቻሉ ገልፀዋል። በአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነትና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ራሄል ፅጌ  አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ጥቆማ የሚሰጥበትን በአንድ ቦታ ያስተናግድ የነበረው የ'905'ን የጥሪ ማዕከል በ40 ቦታ እንዲሰጥና አስቸኳይ ጥገና የሚሰጡ ባለሙያዎች ከአንድ ማዕከል ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። ይህም ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም