በአረንጓዴ አሻራ ቀን በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ላይ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

68
ሰመራ ኢዜአ ሐምሌ13/2011 በአረንጓዴ አሻራ ቀን በአፋር ክልል በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ላይ ህብረተቡ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ ጥሪ አቀረቡ። የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ  በሰመራ  ከተማ  የችግኝ ተከላ አካሄደዋል። በዚህ ስነስርዓት ወቅት ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት ህይወቱ ከእንስሳት ጋር በጥብቅ ለተቆራኘው አርብቶ አደር ህብረተሰብ ለራሱም ሆነ ለእንስሳቱ ህልውና አረንጓዴ ልማት አስፈላጊ ነው። የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ በረሃማነትን ከመከላከል ባሻገር  እንደአፋር ላለ አርብቶ አደር ማህበረሰብ ዛፎች ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለእስሳት ምግብነትና መድሃኒትነት የሚሰጠው  ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። ለዘመናት ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲመነጠሩ የነበሩ ደኖችና ሀገር በቀል ዛፎች እየተመናመኑ በመሆኑ አርብቶአደሩ ህብረተሰቡ በቀላሉ ለድርቅ ተጋለጭ እንዲሆን እያደረጉት ነው። ይህን ችግር ለማቃለል በሀገር ደረጃ በተዘጋጀው ልማት  የአፋር ክልልም ተሳትፎውን በተግባር ለማሳየት ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ   በተለያዩ አካበቢዎች የችግኝ ተካላ እየተካሄደ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል። በተለይም ሐምሌ  22/2011 ዓ.ም  አረንጓዴ አሻራ ቀን የተያዘውን ሀገር አቀፍ ግብ በማሳከት  ታሪክ ለመስራት ችግኝ በመትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ በማልማት ላይ  የክልሉ ህብረተሰብ በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ህብረተሰቡን በማነቃነቅ የራሳቸውን አረንጓዴ አሻራ ለማሳረፍ እንዲሰሩም አመልክተዋል። በክልሉ በዕለቱ እስከ 300ሺህ  ችግኖችን  ለመትከል የቦታ መለየትና  የጉድጓድ ዝግጅት ስራ  እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም