በመፈናቀልና በሌሎች ምክንያቶች ትምህርት ላለፋቸው ተማሪዎች የክረምት ማካካሻ ይሰጣል – ትምህርት ሚኒስቴር

143

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 13/2011 ከቀዬአቸው በመፈናቀልና በሌሎች ምክንያቶች መደበኛ ትምህርታቸውን ያልጨረሱ ተማሪዎች ያለፏቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በክረምት የበጎ ፈቃድ ትምህርት እንደሚያካክሱ ተገለጸ።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶችና መፈናቀል ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ወቅታዊ ችግሮች ሲፈቱና አካባቢዎቹ ሲረጋጉ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ተለይተዋል።

ከእነዚህ መካከል ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ተማሪዎች በሚቀጥለው ዓመት ያቋረጡትን ትምህርት በአዲስ መልክ መማር ይጀምራሉ።

ነገር ግን ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት የወር፣ የሳምንታት ወይም የቀናት ትምህርት ያለፋቸው ተማሪዎች በክረምት የበጎ ፈቃድ ትምህርት ይካካስላቸዋል።

በዚሁ መሰረት “ሶማሌና ደቡብ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ያቋረጡና የተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ያለፏቸውን ተማሪዎች ለይተው ልከውልናል የሌሎችንም እየጠበቅን ነው” ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።

የክረምት የበጎ በቃድ የትምህርት አገልግሎቱ ለተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ያለፋቸውን ትምህርት ማካካስ ተቀዳሚ አላማው መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መረጃዎችን በማሰባሰብ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተማሪዎችና መምህራን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትምህርት ሲሰጡ የስብዕና ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎች የመጡና በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች በስብዕና ግንባታ ላይ እርስ በእርሳቸው እንዲወያዩ እንደሚደረግም አክለዋል።