የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች በሕገ ወጥ ኃይሎች እንዳይጠለፉ ጥንቃቄ መደረግ አለበት - ፓርቲዎች

54
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 13/2011 ዜጎች የሚያነሷቸውን ሕገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ሌሎች ኃይሎች ለጥፋት እንዳይጠቀሙበት ጥንቃቄ እንዲደረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሳሰቡ። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለኢዜአ እንደገለጹት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የክልልነትና ሌሎች የመብት ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊና ተገቢነት ያላቸው ናቸው። ይሁን እንጂ ጥያቄዎቹን የሚደግፉ መስለው አገሪቱን ወደ ብጥብጥ ለማስገባት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚሰሩ ኃይሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሳሳተ መረጃ ሲያሰራጩ እየተስተዋለ መሆኑን ጠቁመዋል። ጥያቄ አቅራቢው አካል ከመንግስት የሚሰጡ ምክንያቶችን በመረዳት ምላሽ እስኪያገኝ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ በርሔ  የይህ "አዲስ መስተዳድር መፍጠር ስለሆነ ፣ ቅይጥ  የሆነ ማህበረሰብ ስለሆነ ያለው እዚያ አካባቢ  የሲዳማ ተወላጆች ብቻ ቢሆኑም የአመለካከት ልዩነት ሊኖር ስለሚችል እነዚህ ሁሉ ወደኋላ ቅሪት ሆነው ሌላ ፀብና ችግር እንዳይፈጥሩ ፅድት ባለ መንገድ የራሱ የሆነ ቴክኒካል ስራዎችን ሰርቶ ክልሏ እንድትመሰረት ማድረግ ስለሚገባው በግልጽ ምርጫ ቦርድ ተናግሯል ማለት ነው። የሲዳማ ጥያቄ የሁሉም ጥያቄ ነው ምክንያቱም ህገ መንግስት መከበር አለበት ነው ያሉት፤ ህገ መንግስት ካልተከበረ እኛም የለንም ስለዚህ እኛም እንደግፋቸዋለን ነገር ግን ስርዓት በያዘ መልኩ ደግሞ መሆን አለበት።" የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው ህዝቡ ጥያቄዎቹን ሲያቀርብም ሆነ ጥያቄዎቹ ከተፈቱ በኋላ የቀድሞ አንድነቱን ባጠናከረ መልኩ መሆን ይኖርበታል ይላሉ። መንግስትም እየቀረቡ ያሉ ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን በህገ መንግስቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን አንቀፆችም ማሻሻል እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። "ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ወዳልተገባ ህገ ወጥ አጀንዳ ለመቀልበስ የሚሰሩ አካላት ስላሉ መንግስትና ህዝብ በጋራ ሊሰሩ ይገባል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሠላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ሰይድ ይመር ናቸው። ህዝቡ በማስመሰል ፖለቲካ ውስጥ የገቡትንና በሃቀኝነት ለመብታቸው የሚከራከሩትን ጠንቅቆ መለየትና 'አስተዋይ መሆን' ይጠበቅበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም