የጋምቤላ ክልለ ሕዝብ በችግኝ ተከላ ያሳየውን ተሳትፎ በእንክብካቤም እንዲያጠናክረው ርዕሰ መስተዳድሩ ጠየቁ

54
ጋምቤላ ሐምሌ 13 ቀን 2011የክልሉ ሕዝብ በችግኝ ተከላው እያሳየ ያለውን ተሳትፎ አንክብካቤ በማድረግ አንዲያጠናክረው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሳሰቡ፡፡ በክልሉ በዘንድሮ ክረምት ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት በደን ለማልበስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገልጿል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ ሕዝብ እንደ አገር የተያዘውን የችግኝ ተከላ ግብ ለማሳካት እያደረገ ያለውን የሚያበረታታ ተነሳሽነትና ተሳትፎ ችግኞቹን በመንከባከብ ሊደግመው ይገባል፡፡ ለዚህም ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም መገናኛ ብዙኃን የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አመልክትዋል፡፡ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኩዌት ሉል እንዳሉት በክልሉ እስካሁን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ሐምሌ 22 የሚካሄደውን የአረንጓዴ አሻራ ቀን በማስመልከት በክልሉ ከ300ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱ መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በተያዘው የክረምት ወቅት 4ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ዕቅድ መያዙንና ከዚህም ውስጥ ሮዳስ የተባለው የሳር ዝርያ፣የፍራፍሬና የጥላ ዛፍ ችግኞች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ቢሮው በክልሉ በ60 ከመቶ በታች የሆነውን የችግኝ የጽድቀት ደረጃ ወደ 95 ከመቶ ለማድረስ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በችገኝ ተከላው ከተሳተፉት መካክል ወይዘሮ ክሮምስ ሊሮ በሰጡት አስተያየት ችግኞች መትከል ብቻውን ግብ ስለማይሆን የተከሏቸውን ችግኞች እንደሚንከባከቡ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ግለሰብ የተከላቸውን ችግኞች የመጽደቅ ሂደት በመከታተል ለታለመላቸው ዓላማ እንዲደርሱ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ "ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ ህጻን ልጅ መከታተልና መቆጣጠር ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አብዱረህማን ሁሴን ናቸው፡፡ በመሆኑም ችግኞችን ተክሎ መሄድ ግብ ያለመሆኑን በመረዳት ሁሉም ኃላፊነት በመውሰድ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ በተያያዘ የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ሠራተኞች በአገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረውን የወሳኝ ኩነቶችን በዓል ምክንያት በማድረግ ለችግኞች ተከላ የሚሆኑ ጉድጓዶች ቆፍረዋል። የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ሰናይ አኩዎር እንደተናገሩት ሠራተኞቹ እንደ አገር የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ ለማሳካት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኤጀንሲው በቀጣይ ሁለት ወራት የችግኝ ተከላ፣የደም ልገሳና ለተማሪዎች ምዝገባ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም