ተመራቂዎች ችግኝ በመትከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ዓላማ እንዲያሳኩ ሚኒስትር ዴኤታው አሳሰቡ

55

ሶዶ ሐምሌ 13 ቀን 2011 (ኢዜአ) ተመራቂዎች ችግኝ በመትከል የአፈርን ለምነት በመመለስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ዓላማ እንዲያሳኩ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ አሳሰቡ።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የተርጫ ካምፓስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተማሪዎች ምረቃን ምክንያት በማድረግ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡

ፕሮፌሴር አፈወርቅ በዚህ ጊዜ እንዳስገነዘቡት ተመራቂዎች የሚተክሉት ችግኝ አገሪቱ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት በማጠናከር የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለምነት እንዲመለስና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያስችላል፡፡

ችግኞቹን በማጽደቅ አረንጓዴ ልማትን ለመመለስ ብሎም ከውጤቱም ተጠቃሚ ለመሆን የዜግነት ግዴታ መወጣት ይገባል ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው መማርና አካባቢን መጠበቅ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውን  ገልጸው፣ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ምረቃውን ምክንያት በማድረግ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር የተላመዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ4ሺህ 500 በላይ ችግኞች መተከላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ችግኞቹን ከመትከል ባሻገር ጸድቀው የሚፈለገውን ውጤት እንዲሰጡ በትዕግስትና ኃላፊነት በተሞላው ስሜት መንከባከብ ተገቢ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ፣በዚህ ረገድ ከተማሪዎች ኅብረትና ከሌሎች አካላት ጋር ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

ችግኞቹ የአካባቢውን ለምነት ከመመለስ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን በመረዳት እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ  ያሳሰቡት ደግሞ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት አለማየሁ ናቸው፡፡

በዞኑ ተከላው ከዘመቻ በዘለለ መልኩ እንደሚከናወን ያወሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ችግኞቹን በመንከባከብና በማጽደቅ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ዘገዬ ገብረመድህን ተማሪዎቹ በችግኝ ተከላው መሳተፋቸው ለአገራዊ ጥሪ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማድረጉን ተናግሯል።

ወደየአካባቢያቸው በሚመለሱበት ወቅትም በተከላው አንደሚሳተፉም  ገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ የአከባቢውን ስነ-ምህዳር መጠበቅ፡የአየር ንብረትን መቆጣጠርና ኢኮኖሚያዊ ጠቄሜታ ያላቸው ማንጎ፣ብርቱካን፣ቡናና ኒም ዛፍ የመሳሰሉ ከ4ሺህ 500 በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨረሲቲ የተርጫ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመርቋል፡፡