የአዳማ ከተማ ልማትና እድገትን ለማፋጠን ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ ቀረበ

81
አዳማ 12/11/2011(ኢዜአ) የአዳማ ከተማን ልማትና እድገት ለማፋጠን ሁሉም በተቀናጀ መልኩ የድርሻውን እንዲያበረክት የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ጥሪ አቀረቡ። የአዳማ ከተማ የዜግነት ግዴታ አገልግሎት መርሀግብርን አስመልክቶ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ዛሬ በከተማዋ ተካሂዷል። መድረኩን የመሩት የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው እንዳሉት  አስተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በተናጥል ሳይሆን በተደራጀ አግባብ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በነጻ መስጠት እንዲችሉ ደንብና መመሪያ በማዘጋጀት ሥራ ውስጥ ተገብቷል። በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪ ከተያዘው የክረምት ወራት ጀምሮ በተቀናጀ መልኩ በመንቀሳቀስ ከተማዋንና አካባቢውን ለመለወጥ እንዲተጋ ጠይቀዋል። በኦሮሞ ባህልና የገዳ ሥርዓት መሰረት አካባቢን መንከባከብ፣ ጠላት ሲመጣ መከላከልና በየደረጃው ያሉ ችግሮችን መፍታት ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም አስታውሰዋል። “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን ባህላችንና ቅርሳችንን በማጣት ለተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እየተጋለጥን ነው” ያሉት ከንቲባው፣ ነባር ባህልንና እሴትን ወደነበረበት ለመመለስ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። የዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት “በከተማዋ የዘመሙ ቤቶችንና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን እናቅና" በሚል መርህ እንደሚካሄድም ከንቲባው አመልክተዋል። የከተማዋ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ከድጃ ጀማል በበኩላቸው የአዳማ ከተማ የዜግነት ግዴታ አገልግሎት መርሀግብርን አስመልክቶ በመድረኩ ላይ ገለጻ አድርገዋል። የዜግነት አገልግሎት ዋና ዓላማ በገዳ ስርዓት መሰረት ዜጎች ለማህበረሰባቸውና ለአገራቸው ተቆርቋሪ ሆነው ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት አብሮ የመስራት ባህልን እንዲያዳብሩ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካል ባለው እውቀት፣ ችሎታና ሃብት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደረግ ጭምር መሆኑንም አስረድተዋል። በተያዘው የክረምት ወራት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ የአካባቢን ንጽህናን የመጠበቅ፣ ችግኝ የመትከል፣ የጎልማሶች ትምህርትን የማጠናከር፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን የመጠገን፣ ደም የመለገስና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች በከተማዋ እንደሚከናወኑም አብራርተዋል። “በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶቹ መሳተፍ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ሊሆን ይገባል” ያሉት ኃላፊዋ ለተሳታፊዎችም እውቅናና ማበረታቻ እንደሚሰጥ አመልክተዋል። አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በመንግስት የተያዘው መርሃ ግብር እየላላ የመጣውን የሃገር ፍቅር ወደ ነበረበት ለመመለስና ሁሉም የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል። የህግ የበላይነት መከበር ለሰላምና ልማት ወሳኝ በመሆኑ ሰላም እንዳይረጋገጥና ሀገራዊ ለውጡን የሚያደናቅፉትን መንግስት እንዲያስቆም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል። በበጎ ፍቃድ የሚሰራው ሥራ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ መሆን እንዳለበት ጠቁመው በዜግነት አገልግሎት በመሳተፍ የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም