በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ በነገሌ ከተማ ወጣቶች ገለጹ

152

ሐምሌ  (ኢዜአ)12/ 2011በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ተሳትፏቸውን በማጠናከር የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በጉጂ ዞን የነገሌ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
በከተማ ወጣቶችና ሌሎች ነዋሪዎች የተሳተፉበትና  በበጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተዘጋጀ ውይይትና የፅዳት ዘመቻ ተካሂዷል።በዚህ ዝግጅት ተሳታፊ ከነበሩት ወጣቶች መካከል የወሎ ዩኒቨርስቲ ሲቪል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ናስር መሃመድ  በሰጠው አስተያየት ባለፈው ዓመት ክረምት ከባልደረቦቹ ጋር የተከለው የፅድ ችግኝ ጸድቆ በማየቱ መደሰቱን ተናግሯል።

” የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተቸገሩ የሚረደዱበትና  የስራ ልምድ የሚገኝበትና ሀገራዊ የዜግነት ግዴታ በመሆኑ ተቀባይነት ያለው የተግባር ስራ ነው “ብሏል።

ከትምህርት መስክ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ቆሻሻን በማጽዳት የእረፍት ጊዜውን ለማሳለፍ  ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የሰላም ፣ የልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ሁሉንም የሚመለከት በጎ ተግባር እንደሆነ አመልክተዋል።

ወጣት በረከት ቦነያ በበኩሉ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአንድ ቀን ብቻ 15 የፅድና የባህርዛፍ ችግኝ መትከሉን ገልጸል።

በቀጣይም እስከ ሁለት መቶ ችግኝ የመትከል እቅድ እንዳለው ገልጾ ” በጎ ተግባሩ ትምህርት ጨርሶ ወደ ስራ ሲገባ ልምድ ሆኖ ያገለግለኛል” ብሏል።

ወጣቶች እንዳሉት በስራው ተሳትፏቸውን በማጠናከር የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

“አካባቢን በማጽዳት ከተላላፊ የጤና ችግሮች እራስን መከላከልና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ባህልና ልምድ ልናደርግ ይገባል” ያሉት ደግሞ   ወይዘሮ አባይ ጌታቸው የተባሉት የከተማው ነዋሪ ናቸው።

ቂምና ጥላቻ ቀርቶ የሰላም ፣የመቻቻልና የአንድነት ባህል እንዲጠናከር የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ውይይቱን የመሩት የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳደሪ አቶ ሮባ ተርጫ”ወጣቱ ከአባቶቹ የወረሰውን የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ፣የመረዳዳትና ማህበራዊ በጎ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል “ብለዋል።

በተያዘው ክረምት በበጎ ፈቃድ አንድ ሰው በቀን አርባ ሁለት በወራት ደግሞ አጠቃላይ በዞኑ 6 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

ዋና አስተዳደርው ወላጆቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 58 ህጻናት ከነገሌ ከተማ በጎ አድራጊዎች የተሰበሰበ 696 ደብተርና እስኪቢርቶ አስረክበዋል።

በውይይቱ የተካፈሉ 1ሺህ 200 የሚሆኑ ወጣቶችና ሌሎችን ነዋሪዎች የነገሌ ሆስፒታልን በማጽዳት ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስኬታማነት   ያላቸውን ተነሳሽነት አረጋግጠዋል።

በክረምት 182 ሺህ ወጣቶች  የሚሳተፉበት የበ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ስራ በዞኑ አናሶራ ወረዳ ትናንት በይፋ መጀመሩን በወቅቱ ተገልጿልል።