ፍርድ ቤቱ ሙስና ወንጀል ተከሳሽ በእስራትና በገንዘብ ቀጣ

82
ሐምሌ 12/ 2011 (ኢዜአ) የመተከል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በሙስና ወንጀል ተከሳሹን በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ወሰነ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በአምስት ዓመት ከአራት ወራት ጽኑ እስራትና የገንዘብ  ቀጣ፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታ ፈንታው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ያስተላለፈው የወምበራ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ደሞዝ ከፋይ በነበረው አቶ አየሩ ቀናው በተባለ ግለሰብ ላይ ነው፡፡ ግለሰቡ በጽህፈት ቤቱ  በሚሰራበት ወቅት ከ80 ሺህ በላይ ብር በከባድ እምነት መጉደል የሙስና ወንጀል መከሰሱን ተናግረዋል፡፡ ግለሰቡ ወንጀሉን መፈጸሙ በዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት በእስራትና አምስት ሺህ ብር ቅጣት እንደወሰነበት ገልጸዋል፡፡ በተያያዘ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩ 12 ሰዎችን በነጻ አሰናበተ ተብሎ ሰኔ 25 ቀን 2011 መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ሆኖም የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ  ሕግ ''የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩ 12 ሰዎችን ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለኝም በሚል ከማረሚያ ቤት እንዲወጡ ውሳኔ አስተላለፈ” በሚል እንዲስተካከል በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት ማስተካከያ መደረጉን አዜአ አስታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም