ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት ሴት የጠፈር ተመራማሪዎች እንዲኖሯት እየሰራን ነው-ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ

3662

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2010 ኢትዮጵያ በመጭዎቹ አስር ዓመታት ሴት የጠፈር ተመራማሪዎች እንዲኖሯት እየሰራ መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ከቴክኖቬሽን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ከተለያዩ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤት የተወጣጡ ሴት ተማሪዎች ለሶፍትዌር ልማት የሚጠቅሙ አዳዲስ ሃሳቦችና የፈጠራ ስራዎች ማቅረቢያ መድረክ አዘጋጅቷል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ሴት የጠፈር ተመራማሪዎች እንዲኖሯት የተለያዩ ፕሮግራሞች ተቀርጸው እየተሰራ ነው።

መንግስትና ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ከሚመድቡት ዓመታዊ በጀት ላይ 20 በመቶውን በዘርፉ ፍላጎት እና የፈጠራ ክህሎት ላላቸው ሴቶች ድጋፍ እንደሚውል ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን የሚያሳድግ ብሎክ ቼን የተሰኘ ዓለም አቀፍ ሶፍት ዌርና ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባታቸውንም ገልጸዋል።

በዚህ ቴክኖሎጂ መሰረትም በመጀመሪያው ዙር 45 ሴቶችን በማሰልጠን የፈጠራ አቅማቸውን ለማሳደግ ማቀዳቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ ላይ ከ10-18 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ85 በላይ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

በ2009 ዓ.ም በተካሄደ የቴክኖሎጂና ፈጠራ ውድድር ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሴት ተማሪዎች ከ10 በላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ የሰሩ ሲሆን በዘንድሮ ዓመትም ከ18 በላይ መተግበሪያዎችን ሰርተው አሳይተዋል።