የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ የጸጥታ እና የሰራዊቱ ውስጣዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዱ

870

ሐምሌ 12/2011 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ የጸጥታ እና የሰራዊቱ ውስጣዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ትናንት ውይይት አካሄደዋል።

ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይታቸው በቅርቡ በተቋሙ አመራሮችና በአማራ ክልል አመራሮች ላይ የደረሰው አደጋ ከፍተኛ ቁጭት የፈጠረ መሆን መግለጻቸውንና ማውገዛቸውን የመከላከያ ዋና ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

አመራሮቹ ድርጊቱ በቀጣይ እንዳይደገም እንደሚሰሩ በውይይቱ ማጠቃለያ ባወጡት ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ ማረጋገጣቸውም ተገልጿል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት የተሰጠውን ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በቁርጠኝነትና ህዝባዊነት በተለበሰ መልኩ እንደሚወጣና የተሰጠውንም ተልዕኮ ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ጸድቶ ለመወጣት እንደሚሰራም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

መከላከያ ሰራዊቱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ውስጣዊ አንድነቱን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን እንደሚታገልም  ተገልጿል።

የተሰው ጓዶች ህልፈት የተቋሙን የሰራዊት አባላት ለቀጣይ ስራ የሚያነሳሳ እንጂ የማይዳክም እንደሆነ  የተገለጸ ሲሆን መከላከያ ሰራዊት ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነም ተጠቁሟል።

በውይይቱ ላይ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሐመድን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እንደተገኙበትና መድረኩ ከምንግዜውም በላይ ከፍተኛ መግባባትና የአንድነት መንፈስ የተፈጠረበት መድረክ እንደነበርም በመግለጫው ተመልክቷል።