በአፋር ክልል የኤች አይ ቪ /ኤድስ ስርጭትን ለመግታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲያድግ ርዕሰ-መስተዳድሩ ጠየቁ

105

ሰመራ ሐምሌ 12 / 2011 በክልሉ እያንሰራራ የሚገኘውን የኤች አይ ቪ /ኤድስ ስርጭትን ለመግታት ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ አሳሰቡ።
የክልሉ ኤች አይ ቪ /ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት 17ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ አካሂዷል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ ጉባዔውን ሲከፍቱ እንዳስገነዘቡት ባለድርሻዎች በሽታው በክልሉ እንዳያንሰራራ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የቫይረሱን ስርጭትን ለመግታት በተጨባጭ በመግታትና የመድኃኒት ተደራሽነትን ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ያስታወሱት አቶ አወል፣በውጤቶቹ የተፈጠረው መዘናጋት በሽታው እንዲያንሰራራ ማድረጉ አመልክተዋል።

ለዚህም  ለቫይረሱ ስርጭት መቀነስ ሚና የተጫወቱት የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሸማግሌዎች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ስርጭቱ በመቀነስ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የፌዴራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌሬዳ ክፍሌ በበኩላቸው የቫይረሱ ስርጭት ለመቀነስ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችና አካባቢዎች ላይ አተኩሮ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

በተጨማሪም ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን አንዲያውቁ  በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ምርመራ ማጠናከርና የመድኃኒት አቅርቦትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የክልሉ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያህያ መሐመድ  በከልሉ እያገረሸ የመጣውን የቫይረሱ ስርጭት ጋር የከፋ ማህበራዊ ችግር አንዳያስከትል ከሴቶችና ከወጣቶችች አደረጃጃቶች አንዲሁም ባህላዊ መሪዎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ የኢትዮ-ጂቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደርና የስኳር ፕሮጀክቶች ያሉበት በመሆኑ የቫይረሱ ስርጭት ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአፋር ክልል ከ12ሺህ በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር አንደሚኖሩ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል።

በከልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምላሽ ስራዎች የቫይረሱ ስርጭት ወደ አንድ ነጥብ አንድ በመቶ ወርዶ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።