የመስኖ ግድብ ሥራ ከበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል መሆኑ ተገለጸ

166

ሐምሌ 12/2011 (ኢዜአ) የመስኖ ግድብ፣ የስንዴ፣ የቡና እና የዶሮ እርባታ ሥራዎች የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

መንግስት የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ለማረጋገጥ በ2012 በጀት ዓመት ተጨማሪ 20 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጎማ ማድረጉ ይታወቃል።

የተጨማሪ በጀት ድጎማው ደግሞ ለግብርና ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን እና ግብርናውን በመለወጥ በቀጣዮቹ ዓመታት አበረታች ሽግግር ለማምጣት ዓላማ ያደረገ መሆኑ መንግስት ማስታወቁም ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመንግስትን የ2012 የትኩረት አቅጣጫዎች በተናገሩበት ወቅት ከተመደበው በጀት ግማሽ ያህሉ ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች የሚውል በመሆኑ ኢኮኖሚውን የሚያረጋጋ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ አስታውቀው ነበር።

ይህን ተከተሎ ለግብርናው ዘርፍ የተመደበው ተጨማሪ የ20 ቢሊዮን ብር በጀት ድጎማ ምን ፋይዳ እንዳለው እና ምን ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚያደርግ ኢዜአ የግብርና ሚኒስትርን አነጋግሯል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፤ ለግብርናው አለመዘመን ዋነኛ ምክንያት ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ የግብርና ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ የአየር ሁኔታው የተዛባና ተለዋዋጭ በመሆኑ ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።

ሁኔታውን በዘላቂነት ለመቀየር የመስኖ ግድቦች ግንባታ መፍትሄ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የሚናገሩት።

የተጨማሪ በጀት ድጎማው የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን ለማሳደግ፣ የስንዴ፣ የቡና ምርቶችን እንዲሁም የዶሮ እርባታን በመላ አገሪቱ ለማሳደግ ያስችላልም  ብለዋል።

በተጨማሪም የበጀት ድጎማው የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማስፋፈት ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች እንዲስፋፉና የግብርና ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ የእርሻ መሳሪያዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ ከውጭ ከሚመጡ የዶሮ ምርቶች ይልቅ ወደ ውጭ የሚላኩ የዶሮ ምርቶችን በማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት አጠቃላይ የተመደበውን በጀትም ሆነ ድጎማው የግብርናውን ዘመናዊነት ለማሻሻል ዓላማ ያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2012 በጀት ዓመት 386 ቢሊዮን 954 ሚሊዮን 965 ሺህ 289 ብር የፌዴራል መንግስት በጀት ማጽደቁ የሚታወስ ነው።