በደሴ ከተማ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በችግኝ ተከላና በደም ልገሳ ተጀመረ

112
ደሴ /ሶዶ  12/11/2011 (ኢዜአ) በደሴ ከተማ አስተዳደር የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በችግኝ ተከላና በደም ልገሳ ተጀመረ። የወላይታ ምሁራን ማህበር አባላትም ከ3ሺህ 500 በላይ ችግኞችን ተክለዋል። በደሴ ከተማ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ዛሬ ሲጀመር የከተማ አስተዳደሩ አዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ጀማል እንዳሉት በአገልግሎቱ ከ61 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞች ይሳተፋሉ፡፡ አገልግሎቱ በችግኝ ተከላ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራት፣ አረጋዊያንን በመረዳትና በመንከባብ፣ አርሶ አደሮችን በማገዝና በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ አቶ መሀምድ እንዳሉት ዛሬ በይፋ በተጀመረው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በከተማው በሚገኘው “መርሆ ግቢ ቤተመንግስት" ግቢ ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ከ40 በለይ የሚሆኑ ሰዎችም ደም ለግሰዋል። የደሴ ከተማ አስተዳደር ግብርና እና መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም ሙስጠፋ በበኩላቸው በተያዘው የክረምት ወራት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ3 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ በመርሆ ግቢ የተተከሉ አገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የእዚሁ አካል መሆናቸውን ጠቁመው “ለችግኞቹ ተገቢ ክብካቤና ጥበቃ በማድረግ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት እንዲጸድቁ ይደረጋል” ብለዋል፡፡ በከተማው አምስት ክፍለ ከተሞችና የገጠር ቀበሌያት በቂ ጉድጓድ ተቆፍሮ ለችግኝ ተከላ መዘጋጀቱንም አቶ አብዱልከሪም ገልጸዋል። የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰለሞን ጌታሁን በአገር አቀፍ ደረጃ በታቀደው መሰረት በክረምት 40 ችግኝ ለመትከል አቅደው በዛሬው ዕለት 10 ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸዋል፡፡ “ችግኞቹ በአግባቡ እንዲጸድቁ ክትትልና እንክብካቤ አደርጋለሁ” ያሉት አቶ ሰለሞን ዛሬ ለ8ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩም ተናግረዋል። ሌላው የፒያሳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኃይለማሪያም ተመልሶ በበኩሉ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመስራትና በመጠገን፣ ደም በመለገስ፣ ችግኝ በመትከልና በሌሎች መሰል ተግባራት ለመሳተፍ መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ ዛሬ በተዘጋጀው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መክፈቻ መርሀ ግብር ላይ 5 ችግኝ መትከሉንና ለ10ኛ ጊዜ ደም መለገሱን ተናግሯል፡፡ “የተከልኳቸውን ችግኞች ተገቢ ትኩረት ሰጥቼ እንከባከባለሁ፤ በየሦስት ወሩም በቋሚነት ደም እለግሳለሁ” ሲልም ተናግሯል፡፡ ዛሬ በይፋ በተጀመረው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዝግጅት ላይ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግስት አመራሮች፣ ወጣቶችና የተለያዩ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና የወላይታ ምሁራን ማህበር አባላት በሶዶ ከተማ ዋራዛ ሾሆ ቀበሌ በመገኘት ችግኝ ተክለዋል። የማህበሩ አባላት ዛሬ የችግኝ ተከላ ሥራ ያከናወኑት በወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው። “የአረንጓዴ ልማትን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ አሻራችንን ማሳረፍ ይገባናል” በሚል መሪ ቃል ባካሄዱት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም የማህበሩ አባላት ከ3ሺህ 500 በላይ ችግኞችን ተክለዋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ወዳጆ እንዳሉት ችግኞቹ የአየር ንብረትን ከመቆጣጠር ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ሃገር በቀል ችግኞች ናቸው። የማህበሩ አባላት ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ጸድቀው የተፈለገውን ጥቅም መስጠት እንዲችሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል። ልማትና ዕድገት ከሠላም ተነጥለው እንደማይታዩ አስታውሰው፣ ማህበሩ በተለያዩ የልማት ሥራዎች በመሳተፍ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል። የወላይታ ሶዶ ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክብረአብ ሴታ በበኩላቸው እንዳሉት በከተማዋ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያካተተ የችግኝ ተከላ መርሀግብር እየተከናወነ ነው። በክረምቱ የችግኝ ተከላ መርሀግብርም ከ5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታስቦ የጉድጓድ ዘግጅትና መሰል ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት። የሚተከሉ ችግኞች የአከባቢውን ስነ ምህዳር የተላመዱ፣ ቶሎ የሚደርሱና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው እንዲሆኑ ጥንቃቄ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በግለሰብ ማሳዎች ከሚተከሉ ችግኞች ባሻገር የልማት ቡድንና ተቋማት ኃላፊነት ወስደው የሚተክሉበትና ክብካቤ የሚያደርጉበት አሰራር መዘርጋቱንም አቶ ክብረአብ አስረድተዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም