በምስራቅ ጎጃምና በአፋር ደን ለማልማት ዓላማውያደረገ የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው

66
ደብረ ማርቆስ/ሰመራ ሐምሌ 12 /2011 (አዜአ)  በምስራቅ ጎጃም ዞን የደን ሽፋን ለማሳደግ የሚረዱ ከ120 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች መተከላቸው የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ ችግኞቹ ካለፈው መጨረሻ  ወር ጀምሮ እስካሁን ኅብረተሰቡን  በማሳተፍ መተከላቸው  ተገልጿል። የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምቱ ወቅት 200 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ። በደን ይዞታዎችና የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራ በተካሄደባቸው ሥፍራዎች ጨምሮ በ27 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተከላው እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። በመተከል ላይ ካሉ ችግኞች ውስጥ 60 በመቶ ያክሉ ዋንዛ፣ ግራር፣ ፅድ፣ ወይራና  ኮሶ ዝርያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ በክረምቱ እየተተከሉ ባሉ ችግኞች የዞኑ የደን ሽፋን አሁን ካለበት 14 በመቶ ወደ 17 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል ። በሰዴ ወረዳ የደብረሰላም ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እንይሽ ፍላቴ ባለፉት አመታት በአካባቢያቸው የተተከሉ ችግኞች በጎርፍ የተረሸሩ ቦታዎች አገግመዋል ። “በአካባቢያችን በተተከሉ ችግኞች ተራቁተው የነበሩ የደን ይዞታዎች እያገገሙ ናቸው” ያሉት ደግሞ በጎንቻ ሲሶ ወረዳ የደብ ረዘይት ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ላቄ ሞላ ናቸው ። በተያዘው ክረምት ቀድመው ባዘጋጇቸው ጉድጓዶች ውስጥ ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ እያንዳንዱ ግለሰብ 40 ችግኝ እየተከለ መሆኑን አስታውቀዋል። ለሚተክሏቸው ችግኞች እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በዞኑ ከ265ሺህ ሄክታር  በላይ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ደን መኖሩ ታውቋል ። በተመሳሳይ በአፋር ክልል የደን ይዞታዎችን መልሶ ለማልማት የችግኝ ተከላ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ እንስሳት፣ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት ተከላው ከአዳዲስ ከተሞች መስፋፋትና ከማገዶ ፍላጎት ጋር ተያይዞ የደን ይዞታዎች በአሳሳቢ ደረጃ የተመናመኑ የደን ይዞታዎች መልሰው ለማገገም ያስችላቸዋል። ተከላው የአካባቢውን የአየር ፀባይ ባገናዘበ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፣ ካለፈው መጨረሻ ጀምሮ ወዲህ 90 ሺህ የዛፍ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል ። እስከ ጥቅምት 2011 ዓም በሚዘልቀው ተከላ 300ሺህ የዛፍ ችግኞች እንደሚተከሉም አቶ መሐመድ አስታውቀዋል። የሰመራ ከተማ ነዋሪ አቶ ኡስማን ያሲን ሰመራን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ የክልሉ ከተሞች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ የደን ይዞታዎች መመናመናቸውን ተናግረዋል ። ይዞታዎቹ እንዲያገግሙ በተከላው እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። “እየተተከሉ ያሉ ችግኞች እንዲጸድቁ በሚደረገው የእንክብካቤ ስራ ለመሳተፍ ወስኛለሁ“ ያሉት ደግሞ የሎጊያ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ ኢብራሂም ናቸው ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም